በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ህወሓት የምርጫ ቦርዱን የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ውሳኔ እንደማይቀበል አስታወቀ


የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አርማ
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አርማ

“የሰላም ስምምነቱን ስለሚፈታተን ተመርምሮ ይስተካከል”-ጊዜያዊ አስተዳደሩ

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ ስለ ፓርቲው የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበልና ይነሣልኝ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ ውድቅ ማድረጉን ተቃውሟል::

ህወሓት በመግለጫው፣ የቦርዱ ውሳኔ፥ የፕሪቶርያውያን የሰላም ስምምነት እና ሕግን መሠረት ያላደረገ ነው፤ በማለት እንደማይቀበለው አስታውቋል::

የፕሪቶርያው ስምምነት ማዕከሉ፥ ሰላም፣ ሰብአዊ መብት፣ ዴሞክራሲ፣ ተጠያቂነት እና ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐት መመለስ ነው፤ ያለው ህወሓት፣ ይህን ስምምነት በመተግበር ረገድ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በተናጠል እና በጋራ ግዴታቸውን እየፈጸሙ እንደሚገኙ ገልጿል::

ኾኖም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ የህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ እንዲነሣ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ ያደረገው፣ ከሰላም ስምምነቱ ውጪ በኾነ አካሔድ እንደኾነ ህወሓት ተችቷል፡፡ የቦርዱ ውሳኔ፥ የሰላም ስምምነቱን የማይቀበል፣ እየተጠናከረ የመጣውን የስምምነቱን ትግበራ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ እንዲሁም ከጦርነት ወደ ሰላማዊ ትግል የሚመለሱ የፖለቲካ ኃይሎችን ከማበረታታት ይልቅ የሚያፈርስና ዘላቂ ሰላም የማያመጣ ነው፤ በማለት ተቃውሞውን አስረድቷል፡፡

በቀጣይም፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ እንደሚወያይበት ያመለከተው ፓርቲው፣ ቦርዱ ውሳኔውን ዳግም እንዲያጤነው ጠይቋል፡፡ በጉዳዩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የአፍሪካ ኅብረት እገዛ እንዲያደርጉለት ህወሓት በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ጉዳይ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም መግለጫ አውጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ፣ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የኾነው ህወሓት፣ ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ ያስተላለፈው ውሳኔ እንደኾነ ጠቅሶ፣ ውሳኔው፣ በሕግም በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም፤ ብሏል፡፡

የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ፣ የቦርዱ ውሳኔ፥ ህወሓትን ወክለው በትግራይ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ለሚሳተፉት ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች እውቅናን በመንፈግ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጠቅላላ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል፣ እንዲሁም የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን ነው፤ በማለት ተቃውሞታል::

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የሰላም መንገድ ለመደገፍ፣ ሕግን፥ በአዎንታዊ የትርጉም ሥርዐት ከመረዳት ይልቅ፤ ቴክኒካዊ በኾነ አረዳድ፣ ሰላማዊ ፖለቲካዊ መግባባትን ማደናቀፍ አይኖርበትም፤ ሲል፣ ቦርዱ ውሳኔውን መርምሮ እንዲያስተካክል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠይቋል::

XS
SM
MD
LG