በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ይነሳልኝ ጥያቄ በምርጫ ቦርድ ውድቅ ተደረገ


የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አርማ
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አርማ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው የሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ቦርዱ አስታወቀ።

ሕጋዊ ሰውነቱን ይዞ ለመቀጠል በአዋጁ መሰረት በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብና፣ ቦርዱም ሕጉ መሰረት አድርጎ ሲፈቅ መኾኑን ቦርዱ ገልጿል።

የህወሓት ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሓላፊ አቶ ተወልደ ገብረፃድቃን ፓርቲያቸው በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ምላሽ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል::

ህወሓት ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፃ ተግባር ላይ መሳተፉን ማረጋገጡን ጠቅሶ፣ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲሰረዝ፣ ጥር 10/ 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስተላለፈው ውሳኔ፤ የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም እንዳይንቀሳቀሱ ፣ የፓርቲው ንብረት ህወሓት ዕዳ ካለበት እንዲከፍል እና የቀረው ንብረት ለሥነ ዜጋና ለመራጮች ትምህርት እንዲውል ወስኖ ነበር።

ህወሓት ሚያዝያ 28/ 2015 ዓ.ም ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ ፤ ትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት በሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ መንገድ እንዲፈታ ፓርቲው ከፌደራሉ መንግሥት ጋራ ስምምነት ላይ መድረሱን ጠቅሶ፤ የቦርዱ የቀደመ ውሳኔ እንዲነሳለት መጠየቁን ቦርዱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ቦርዱ ትላንት ግንቦት 4/ 2015 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የፓርቲውን ጥያቄ መመርመሩን እና የቀደመ ውሳኔው አዋጅን መሰረ አድርጎ የተወሰነ መኾኑን ገልጾ፣ “ምንም እንኳን በደብዳቤው ላይ እንደተገለፀው ለቦርዱ ውሳኔ መሰረት የሆነው ኃይል መሰረት ያደረገ የአመፃ ተግባር አሁኑ ባይኖርም እንደገና ሕጋዊ ሰውነቱን ለፓርቲው ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1162/2011 ላይ ተደንግገው አይገኙም” ብሏል።
አክሎም የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት የማስመለስ ጉዳይ በሕግ የተደገፈ ኾኖ ስላላገኘው ጥያቄውን እንዳልተቀበለው አስታውቋል።

ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ይዞ መንቀሳቀስ የሚችለው በአዋጁ መሰረት በድጋሜ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብና፣ ቦርዱ ሕጉ መሰረት አድርጎ ሲፈቅድ መኾኑን ገልጿል።

እንዲሁም የፓርቲው አመራሮችና የንብረት ጉዳይን በተመለከተ የስረዛ ውጤት በመኾኑ እንደ አዲስ ሊጠየቁ የሚችሉ ኾነው እንዳልተገኙ ቦርዱ ገልጿል::

የቦርዱን ውሳኔ በተመለከተ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የህወሓት ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሓላፊ አቶ ተወልደ ገብረፃድቃን፤ ፓርቲያቸው በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ምላሽ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል::

በተመሳሳይ ዜና በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሳልሳይ ወያነና ባይቶና የተባሉ ፓርቲዎች የመስራች ጉባኤ እንዲያካሂዱ መወሰኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ደብዳቤ ገልጿል::

XS
SM
MD
LG