በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ጦር አዛዥ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የባንክ ሒሳብ አገዱ


የሱዳን ጦር አዛዥ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የባንክ ሒሳብ አገዱ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:20 0:00

የሱዳን ጦር አዛዥ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የባንክ ሒሳብ አገዱ

  • በግጭቱ የመፍትሔ አማራጮች ከተመድ ተቋማት ጋራ ተወያይተዋል

የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ጀነራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን፣ በተፋላሚያቸው በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል(RSF) ስም የተመዘገቡ የባንክ ሒሳቦች በሙሉ እንዲታገዱ ትእዛዝ ሰጥተዋል።

ላለፈው አንድ ወር፣ በመላው ሱዳን እየተዋጉ የሚገኙት ሁለቱ ኃይሎች፣ በርካታ ችግሮች ያሉባትን ሀገር ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንድትገባ እየገፏት ነው።

ጀነራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን፣ እሑድ ዕለት ያስተላለፉት ዐዋጅ በዋናነት ያነጣጠረው፣ በሱዳን ባንኮች ውስጥ፣ በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ስም በተከፈቱ እና የቡድኑ ንብረት የኾኑ ድርጅቶች በሚያንቀሳቅሷቸው የባንክ ሒሳቦች ላይ እንደኾነ፣ የሀገሪቱ ብሔራዊ የዜና ማሠራጫ “ሱና” ዘግቧል።

ኾኖም፣ የባንክ ሒሳብ እገዳው፣ በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሉ ላይ፣ ምን ዐይነት ቀጥተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ወይም ቡርሃን ያስተላለፉት ትእዛዝ በምን መልኩ ተፈጻሚ እንደሚኾን እስከ አሁን ግልጽ አይደለም። ከባንክ እገዳው በተጨማሪ፣ የጦር አዛዡ፥ የሱዳን ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የነበሩትን አንሥተው በሌላ መተካታቸውም ተገልጿል፡፡ ይህም፣ ምናልባት ከእገዳው ጋራ ግንኙነት ሳይኖረው እንደማይቀር ተገምቷል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፣ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ፣ የሱዳን የገንዘብ ተቋማትንና የወርቅ ክምችቶችን በመግዛቱ፣ በጊዜ ሒደት በርካታ ንብረት ማፍራት እና ማከማቸት ችሏል።

ሁለቱ ተቀናቃኞች፣ ከሚያዝያ ወር አጋማሽ ጀምሮ በገቡበት ግልጽ የሥልጣን ፍልሚያ የተነሣ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲሰደዱ አድርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሱዳን ባለሥልጣናት፣ በሀገሪቱ ያለውን ግጭት መፍታት በሚቻልበት መንገድ እና በሰብአዊ ርዳታው አሰጣጥ ዙሪያ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ተወካዮች ጋራ ተወያይተዋል።

የሱዳን የገንዘብ ሚኒስትር ጂብሪል ኢብራሂም፣ በሱዳን የመንግሥታቱ ድርጅት ተወካይ ከኾኑት ቮልከር ፐርትስ ጋራ፣ የውኃ እጥረትን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

“የግብርና ወቅቱን በተመለከተና በመጪው ዓመት የምግብ እጥረት እንዳያጋጥመን፣ የግብርናውን ወቅት መደገፍ ምን ያህል አስፈላጊ እንደኾነ ተነጋግረናል፤” ያሉት ፐርትስ፣ “በፖርት ሱዳን ስላለው የውኃ እጥረትም ተወያይተናል፡፡ በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች፣ በዚኹ የውኃ እጥረት ምክንያት ከመላ ሀገሪቱ ወደ ፖርት ሱዳን እየሔዱ ናቸው። አሁን የበጋ ወቅት እየገባ ነው፡፡ ያ ማለት የውኃ እጥረት ይኖራል። ስለዚኽ በፖርት ሱዳን ያለውን የውኃ ችግር በመፍታት፣ ቢያንስ ለመጪው ወቅት በጊዜያዊነት እንዲያግዙን ጠይቀናቸዋል፤” ብለዋል።

ውይይቱ በባለሥልጣናቱ መካከል የተካሔደው፣ በጦርነት ከምትታመሰው ዋና ከተማዋ ካርቱም እና ከሌሎችም አካባቢዎች የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች ተሰድደው በሚገኙባት ፖርት ሱዳን ከተማ ነው። ልዩ ልዩ የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማት፣ መድኃኒት በማቅረብ እና ውኃ በማጣራት እያደረጉ ያለውን ጥረት አንሥተው መወያየታቸውን የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ ሰብአዊ ችግሩን ለመቅረፍ፣ ተቋማቱ ተጨማሪ ድጋፎችን እንዲያደርጉ መጠየቃቸውንም አመልክተዋል።

“ነገሮች በጥሩ ኹኔታ እየሔዱ ነው፤ የበለጠ እንዲያደርጉም ጠይቀናቸዋል፤” ያሉት ሚኒስትሩ፣ የተመድ ተቋማቱም አሉብን ያሏቸውን ችግሮች ማዳመጣቸውን ገልጸዋል፤ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ፣ እነዚያን ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንሠራለን፤” ሲሉ አመልክተዋል፡፡

በሱዳን ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ አገሪቱ ትርምስ ወስጥ ገብታለች። ዋና ከተማዋ ካርቱም፣ ወደ ጦር አውድማነት ስትቀየር፣ ምዕራባዊው የዳርፉር ክልል ደግሞ፣ የሰዎችን ሕይወት እያጠፉ ባሉ የጎሣ ግጭቶች እየተናጠች ነው። በዚኽ ግጭት፣ ንጹሓን ዜጎችን ጨምሮ፣ እስከ አሁን ከ600 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች፣ የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይልን፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እና የጅምላ ዝርፊያ በመፈጸም ሲከሡ፣ የጦር ኃይሉን ደግሞ በንጹሐን ዜጎች መኖሪያ አካባቢ ያለልዩነት የቦምብ ድብደባ በማካሔድ ይወነጅላሉ።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፣ ሁለቱም ኃይሎች ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢያደርጉም፣ ሁሉም ስምምነቶች ሳይጸኑ ተጥሰዋል። ሁለቱም ተፋላሚዎች፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመፈጸምም እርስ በርስ ይወነጃጀላሉ።

ባለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ ሁለቱም ተፋላሚዎች፣ ግጭቱን ሸሽተው ለሚሰደዱ ሰላማውያን ሰዎች፣ አስተማማኝ መተላለፊያ እንዲኖርና በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ለሚከናወኑ የሰብአዊ ተራድኦ ተግባራት ጥበቃ እንዲደረግ፣ የሳዑዲ አረቢያ ከተማ በኾነችው ጀዳ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ይኸው ስምምነት፣ ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲቀየር፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ዓለም አቀፍ ጥረት እንደቀጠለ ነው።

XS
SM
MD
LG