በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳኑ ግጭት የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ድርድርን ሊያዘገየው እንደሚችል ተጠቆመ


የሱዳኑ ግጭት የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ድርድርን ሊያዘገየው እንደሚችል ተጠቆመ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:15 0:00

በሱዳን እየተካሔደ ያለው ውጊያ፤ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያካሒዱትን ድርድር ቢያዘገየውም፣ በሕዳሴ ግድቡ አሞላል ላይ ግን ምንም ዐይነት ተጽእኖ እንደማይኖረው፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ(ዶር.) አስታወቁ። አምባሳደር ስለሺ ይህን የተናገሩት፣ “How this Happened - Demystifying the Nile” በሚል ርእስ ለኅትመት የበቃ መጽሐፍ በተመረቀበት ወቅት ነው።

የተፋሰሱን ትስስሮች የሚያሳየው “የዓባይ እውነታዎች” መጽሐፍ ተመርቋል

በሱዳን ጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል መካከል እየተካሔደ ያለው ውጊያ፤ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያካሒዱትን ድርድር ቢያዘገየውም፣ በሕዳሴ ግድቡ አሞላል ላይ ግን ምንም ዐይነት ተጽእኖ እንደማይኖረው፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ(ዶር.) አስታወቁ።

አምባሳደር ስለሺ ይህን የተናገሩት፣ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ያሉ ታሪካዊ ኹነቶችን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና የግል ምልከታዎችን የያዘው፥ “How this Happened - Demystifying the Nile” በሚል ርእስ ለኅትመት የበቃ መጽሐፍ በተመረቀበት ወቅት ነው። በምረቃው ላይ የተገኙት የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዴቪድ ሺን፣ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የዓለም ኃያል ሀገራት፣ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ታሪካዊ ተጽእኖ ተንትነዋል።

ባለፈው ሳምንት፣ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ በተከናወነው የመጽሐፉ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው በተካሔደው ውይይት ላይ የተሳተፉት፣ በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ እንደተናገሩት፣ ከሦስት ሳምንት በላይ ያስቆጠረው የሱዳኑ ግጭት፣ በኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አሞላል እና የሥራ ሒደት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ባይኖርም፣ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ፣ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል የሚደረገውን ድርድር ግን ሊስተጓጎል እንደሚችል አመልክተዋል።

በሱዳን የተፈጠረው ኹኔታ የተጠበቀ እንዳልኾነ የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ “እንዲህ ዐይነት ኹኔታ ድርድሩን ያዘገየዋል፤” ሲሉ፣ ያሳድረዋል ያሉትን ተጽእኖ አስረድተዋል፡፡ አምባሳደር ስለሺ አያይዘውም፣ ግጭቱ ይቀጥላል የሚል እምነት እንደሌላቸውና ሱዳናውያን ወደ መደበኛ ኑሯቸው በቅርቡ እንደሚመለሱ ተስፋቸውን በመግለጽ፣ “ያ ሲኾን ወደ ድርድሩም እንመለሳለን፤” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ያስታወቀችው፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነሐሴ ወር ላይ ሲኾን፣ አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 91 ከመቶ መጠናቀቁን አምባሳደር ስለሺ አመልክተዋል።

በሦስቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው ድርድር፣ አሁንም በአፍሪካ ኅብረት በኩል መቀጠሉን ያመለከቱት አምባሳደር ስለሺ፣ እስከ አሁን ግን ይህ ነው የሚባል ውጤት ላይ አለመደረሱን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ፣ “በሌላው ላይ ጉዳት ሳያስከትል የሚካሔድ ፍትሐዊ አጠቃቀም” በሚል መርሕ መሠረት፣ የሕዳሴ ግድቡን ቀሪ ግንባታ እና አሞላል በማከናወን ላይ እንዳለች አስገንዝበው ቀሪው፥ ሦስቱ ሀገራት ወደፊት፣ የዓባይን ወንዝ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ የሚመለከተው ድርድር መኾኑንና እርሱም ሱዳን ወደ መረጋጋት ስትመለስ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።“በድርድሩ የሚቀረው ነገር፣ እንዴት ወደፊት መሔድ እንደሚቻል ነው። ታላቁ የሕዳሴ ግድብም ኾነ በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች፣ ከቀጣይ የልማት ሥራዎች ጋራ መቀላቀል የለበትም፤” ብለዋል፡፡

“How this Happened - Demystifying the Nile” ወይም “የዓባይ እውነታዎች” የተሰኘው መጽሐፍ ጸሐፊ፣ የጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ መምህር እና በፍሎሪዳ ዩንቨርሲቲ የሳውዝ ኢስት አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት የኾኑት ዶር. ደረጀ በፈቃዱ ተሰማ ናቸው። መጽሐፉ፣ ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንሥቶ፣ የኑቢያ፣ የግብፅ እና የኢትዮጵያ ነገሥታት፣ በዓባይ ዙሪያ የነበራቸውን ግንኙነት፤ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ጨምሮ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታሪክ የቀየሩ ዓለም አቀፍ ክሥተቶችን፣ በዓባይ ዙሪያ የተደረጉ ድርድሮችን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ሳይንሳዊ ሒደቶችን አካትቶ ይዟል።

ዶር. ደረጀ፣ በ526 ገጾች በተቀነበበው መጽሐፋቸው፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሳያገኙ፣ በኩራዝ በአደጉበት በአምቦ ከተማ ካሳለፉት ሕይወት ተነሥተው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ እንዲገነባ ያደረጉ ታሪካዊ ክሥተቶችን፣ የቅርብ እና የሩቅ ሀገራትን ጫና፣ ቀጣናዊ እና የውኃ ፖለቲካ ሚዛን ለውጦችን፣ እንዲሁም ውሳጣዊ ግጭቶችን ዳስሰዋል። በመጽሐፉ ምረቃ ላይ በአደረጉት ንግግር፣ የሕዳሴ ግድብ፥ ዛሬም በጨለማ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተስፋ መኾኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ በጣም እንደሚያስፈልግ ጸሐፊው ገልጸው፣ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅና የኤሌክትሪክ ብርሃን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲዳረስ ማድረግ፣ አገሪቱን የሚያዘምን መሠረታዊ ርምጃ ነው፤ በሚል ብዙዎች የሚሟገቱለት አቋም እንደኾነ አስረድተዋል። “የሕዳሴ ግድቡን በጎበኘኹበት ወቅት፣ ከአሰብኹት በላይ የገዘፈ መኾኑ አስገርሞኛል፤” ሲሉ አድናቆታቸውን ያክላሉ፡፡

ዶር. ደረጀ፣ በመጽሐፋቸው መጨረሻ ያካተቱትን የግል ምልከታ ለመጻፍ፣ የጥቁር እና ነጭ ዓባይ መነሻ ከኾኑት ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ተነሥተው እስከ መዳረሻው የሜዲትራኒያን ባሕር ድረስ ተጉዘዋል። በጉዟቸው ባለፉባቸው ሀገራት የሚኖሩ ሕዝቦች፣ ከዓባይ ጋራ ያላቸውን ቁርኝትም መዝግበዋል።

“የዓባይ እውነታዎች” መጽሐፍ፥ በሌሎች ባለሞያዎች፣ ስለ ዓባይ የተጻፉ ታሪኮችን ከመያዙም በተጨማሪ፣ በመጨረሻው ምዕራፉ፣ በየሀገሩ ከሚኖሩ ሕዝቦች እና አስጎብኚዎች ጸሐፊው ያዩትንና የሰሙትን አካትቷል። እነዚያን በአካል ተገኝተው የጎበኟቸውን ሰባት ሥፍራዎች ሲዘረዝሩም፤ የጥቁር ዓባይ ምንጭ የኾነውና ከጣና በስተደቡብ 164 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ሰከላ ወረዳ የሚገኘው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ፣ የጣና ሐይቅ፣ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ዩጋንዳ ውስጥ የሚገኘው ጂንጃ የተሰኘ የነጭ ዓባይ መነሻ ሥፍራ፣ አልሞግራንድ የተሰኘው ሁለቱ ዓባዮች ካርቱም ውስጥ የሚገናኙበት ሥፍራ፣ ካይሮ፣ አሌክሳንደሪያ እና በመጨረሻ ዓባይ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር የሚገባበት ቦታ እንደኾኑ አስፍረዋል፡፡

“የዓባይ እውነታዎች” መጽሐፍ፣ ከታሪካዊ ኹነቶች ባሻገር፣ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ የሚታየውን ኢፍትሐዊ አጠቃቀምና በቅኝ ግዛት ወቅት እንግሊዝ ከነበራት ጣልቃ ገብነት አንሥቶ እስከ አሁን የሚታዩ ዓለም አቀፍ ተጽእኖዎችን አጉልቶ ያሳያል።

ከመጽሐፉ ምረቃ ጋራ በተያያዘ በተካሔደ የፓናል ውይይት ላይ የተካፈሉት፣ በኢትዮጵያ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዴቪድ ሺን፣ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት እና ሌሎች የዓለም ኃያላን ሀገራት፣ በዓባይ ውኃ አጠቃቀምም ኾነ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በታሪክ የነበራቸውን ሚና አብራርተዋል፡፡ በተለይ ዩናይትድ ስቴትስ በዓባይ ዙሪያ ያላት ፖሊሲ፣ ሥልጣን ላይ ከሚወጣው መንግሥት ጋራ አብሮ የሚቀያየር መኾኑን አሥምረውበታል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከትራምፕ አስተዳደር በፊት እና ከትራምፕ አስተዳደር በኋላ በዓባይ ጉዳይ ላይ የምታራምደው ፖሊሲ፣ ግልጽ ልዩነት እንዳለው የሚያነጻጽሩት አምባሳደር ሺን፣ ከዚያ በፊት በዓባይ ጉዳይ ላይ የነበረው ፍላጎት በጣም ዝቅተኛ እንደነበር አውስተዋል። እ.አ.አ ከ1996 እስከ 1999 በኢትዮጵያ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት፣ ክሊንተን፣ ቢያንስ ዓባይ እንዴት የግጭት መንሥኤ ሊኾን እንደሚችልና በአሜሪካ ፍላጎት ላይ ሊያሳድር ስለሚችለው ተጽእኖ ትኩረት እንዲያደርጉ ተደጋጋሚ ግፊት ቢያደርጉም፣ መንግሥታቸው ግን ምንም ፍላጎት አልነበረውም፡፡

ምናልባት በወቅቱ፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያም ኾነ ከግብጽ ጋራ ጥሩ ግንኙነት ስለነበራት፣ መሀል መግባቱን ስላልፈለገች ሊኾን እንደሚችል አስተያየት የሰጡት አምባሳደሩ፣ እስከ ትራምፕ ድረስ የነበሩት አስተዳደሮችም ተመሳሳይ አቋም እንደነበራቸው ገልጸዋል። ትራምፕ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ግን፣ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ በቀጥታ በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት፣ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ጉዳዩን እንዲያሸማግሉ መሾማቸውን ተናግረዋል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩትና በሕዳሴ ግድብ ድርድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚደራደሩ ከፍተኛ ባለሞያዎችን በመምራት የሚሳተፉት አምባሳደር ስለሺም እንዲሁ፣ ከውጭ የሚመጡ ተጽእኖዎች፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን የመጠቀም መብት እንደሚጋፉ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት፣ ከ65 ሚሊየን በላይ የሚኾነው ሕዝቧ ኤሌክትሪክ እንደማያገኝ የምትገልጸው ኢትዮጵያ፣ 85 ከመቶ የሚኾነው የዓባይ ውኃ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ኾኖ ሳለ፣ ውኃውን እንዳትጠቀም መደረጓ፣ ፍትሐዊ አለመኾኑን በተደጋጋሚ ትገልጻለች። 90 ከመቶ የሚኾነውን የውኃ አቅርቦቷን ከዓባይ የምታገኘው ግብጽ በበኩሏ፣ የውኃ መጠኑ ከቀነሰ አደጋ ላይ እወድቃለኹ፤ በሚል፣ ኢትዮጵያ ያለአስገዳጅ እና አሳሪ ስምምነት ግድቡን መሙላት መቀጠሏን ትቃወማለች።

ሁሉም የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት፣ ውኃውን በፍትሐዊነት መጠቀም ይችላሉ፤ የሚሉት አምባሳደር ስለሺ፣ ዶር. ደረጀ በመጽሐፋቸው፣ እነዚኽን ሁሉ ውስብስብ እና የተሳሰሩ የዓባይን እውነታዎች በዝርዝር ማካተታቸው፣ የዓባይን ትክክለኛ ገጽታ ለማሳየት ይጠቅማል፤ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በመጽሐፉ ምረቃ ላይ የተገኙ ሌሎች ምሁራንና ተመራማሪዎችም፥ ዘላቂ ልማት፣ ፍትሐዊ አጠቃቀም እና የዓባይ ወንዝ ልማትን በሚመለከቱ ፖሊሲዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራትን ያማከለ የውኃ አጠቃቀም ማሕቀፍ ጥናት እና በመጪዎቹ ዓመታት፥ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሕዝብ ብዛት እና የፖለቲካ ኹኔታ በዓባይ ውኃ እና አጠቃቀም ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖም ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በእንግሊዝኛ ተጽፎ ለምረቃ የበቃው መጽሐፉ፣ ወደ ዐማርኛ እና አረብኛ ቋንቋዎች እየተተረጎመ መኾኑንና በቅርቡ ለሕዝብ እንደሚደርስም፣ ጸሐፊው ዶር. ደረጀ በፈቃዱ ተሰማ ነግረውናል።

XS
SM
MD
LG