በሱዳን ያሉ ተፋላሚ ወገኖች ከሁለት ሳምንት በፊት የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማስቆም እና ድርድር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት በዛሬው ዕለት ለሮይተርስ አስታውቀዋል፡፡ በሱዳን ውጊያው አሁን የቀጠለ ቢሆንም ይሄ ሁኔታ ግን ተስፋን አጭሯል።
በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ተወካይ ቮልከር ፐርቴስ፤ ሁለቱ ወገኖች ለድርድር ተወካዮቻቸውን መምጣቸውን አስታውቀዋል። ምንም እንኳን እንዴት እንደሚጓዙ ባያስታውቁም ድርድሩ ግን በጄዳ ፣ሳዑዲ አረቢያ ወይም በደቡብ ሱዳን ጁባ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ እስኳሁን ድረስም የተቆረጠ ቀን የለም ነው ያሉት።
ምንም እንኳን እሳቸው ይሄን ቢሉም የሁለቱም ወገን መሪዎች ቀርቦ የመደራደር ተስፋ እስካሁን የጨለመ ይመስላል። አርብ ዕለት የጦሩ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን በነበራቸው ቃለ ምልልስ ከፈጥኖ ደራሽ ቡድኑ እና "አማፂ" ሲሉ ከጠሯቸው ከጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ጋር በጭራሽ ለድርድር እንደማይቀመጡ አስታውቀዋል። በሌላ በኩል ሔመቲ ድርድር የሚኖረው ሙሉ ለሙሉ የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በተያያዘ የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ የድርጅቱ ሰራተኞ ሁኔታዎች ባፈቀዱባቸው አካባቢዎች በሙሉ ምግብ እና የጤና እርዳታ እያቀረቡ እንደሆነ አስታውቀዋል። የአለም የጤና ድርጅት መሰረታዊ መድሃኒቶች፣ የደም ቦርሳዎችን፣ የቀዶ ጥገና መሳሪያዎች ደህንነቱ እስከተረጋገጠ ድረስ ማቅረብ እንደሚችል አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም ተጨማሪ የመድሃኒት አቅርቦት በሱዳን ወደብ ላይ መድረሱንም ጨምረው ገልጸዋል።
በተያያዘ ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ በስደት የገቡ 120,000 ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ በጣም አጣዳፊ የሆነ የድንገተኛ መጠለያ፣ ምግብ እና የንጹህ ውሃ ፍላጎቶች አሏቸው ሲሉ ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።