“ሀገራዊ ሁከት እና ብጥብጥ በመፍጠር፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል ለመናድ በመንቀሳቀስ ወንጀል ጠርጥሪያቸዋለኹ፤” በማለት፣ ፖሊስ፣ በረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቼው ሥር የክሥ መዝገብ የከፈተባቸው አምስት ግለሰቦች፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል፡፡
በክሥ መዝገቡ ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙቱ አምስቱ ግለሰቦች፥ በመምህርነት፣ በበጎ አድራጎት አገልግሎት እና በግል ሥራ ላይ ተሠማርተው የሚገኙት፥ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቼው፣ ፕሮፌሰር ማዕርጉ ቢያበይን፣ ኄኖክ ዐዲሱ፣ ሰሎሞን ልመንህ፣ እንዲሁም የባልደራስ ምክትል ፕሬዚዳንት የኾኑት አቶ አምኃ ዳኘው ሲኾኑ፣ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ከተገለጸ ወዲህ ዛሬ ችሎት የቀረቡት ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡
ፖሊስ በፍርድ ቤት በተፈቀደለት ያለፉት ስምንት ቀናት፣ አከናወንኹ ያላቸውን የምርመራ ሥራዎች ለችሎቱ አቅርቦ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው፣ ለፖሊስ ተጨማሪ ቀን ሊሰጥ አይገባም፤ ብለው መከራከራቸውን፣ ከጠበቆቻቸው አንዱ ሰሎሞን ገዛኽኝ ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው፣ “የባንክ ቤት ማስረጃዎችንና የኤሌክትሮኒክስ ውጤት ማስመጣት” የሚሉ ጉዳዮች በምክንያትነት ካቀረባቸው ውስጥ እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡ ጠበቆች በበኩላቸው፣ እነዚኽ መረጃዎች፣ ከመንግሥት ተቋማት የሚመጡ በመኾናቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢፈቱ ሊያሳድሩ የሚችሉት ምንም ዐይነት ተጽዕኖ እንደማይኖር ጠቅሰው መከራከራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በፖሊስ የቀረበው ሌላው መከራከሪያ፣ “ተጠርጣሪዎቹ በዐማራ ክልል አሥነስተዋል” ባለው ሁከት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ለመመርመር፣ “የምርመራ ቡድን ልከን ውጤቱ እስኪመጣ ድረስ” በእስር ላይ እንዲቆዩ የሚጠይቅ ነው፡፡ የተከሣሽ ጠበቆችም፣ “በዐማራ ክልል ሁከት የተነሣው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ነው፤ በመኾኑም፣ ይህ ጉዳይ ዋስትና ሊያስከለክላቸው አይገባም፤” ብለው ተከራክረዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፣ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ፣ በዋስትናው ጉዳይ ብይን ለመስጠት፣ ለፊታችን ዓርብ ሚያዝያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የዩቲዩብ እና ሌሎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ባለሞያዎች ዳዊት በጋሻው እና ቴዎድሮስ አስፋው፣ ከ10 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በኋላ ትላንት ለሁለተኛ ጊዜ ችሎት ቀርበው፣ እያንዳንዳቸው በ20 ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈቱ ተወስኗል፡፡ ይኹን እንጂ ጠበቃ ሰሎሞን እንዳሉት፣ የዋስትናው ክፍያ ተከፍሎ የመፍቻ ትዕዛዝ ለፖሊስ ጣቢያ ከቀረበ በኋላ፣ ፖሊስ በችሎቱ ውሳኔ መሠረት ሳይለቃቸው፣ ዛሬ ይግባኝ ጠይቋል፡፡
ፖሊስ፣ ለፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ላቀረበው ይግባኝ፣ ነገ ምላሽ እንደሚሰጡና ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅም ጠበቃው ጠቁመዋል፡፡ “ኢትዮ ንቃት” በተሰኘ የዩቲዩብ ማኅበራዊ መገናኛ አዘጋጅ፣ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በመስጠት የምትታወቀው መስከረም አበራ ደግሞ፣ ከትላንት በስቲያ፣ ሚያዝያ 16 ቀን ችሎት ቀርባ፣ ለፖሊስ ተጨማሪ 10 ቀን እንደተፈቀደለት ለማወቅ ተችሏል፡፡