በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሚዲያ ጥፋት የተጠረጠሩ ታሳሪዎች ያለ ቅድመ ኹኔታ እንዲለቀቁ ኢሰመኮ ጠየቀ


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

በዚህ ወር ውስጥ ብቻ በጥቂቱ ዘጠኝ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲሁም የሚዲያ ዐዋጁን በሚጻረር መልኩ መታሰራቸውን የኢትዮጵያ ሰባአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል።

ከሚዲያ ባለሙያዎች በተጨማሪ “በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት ላይ ያነጣጠረ” ያለው “የዘፈቀደ እስርና ወከባ” እንዲቆምም ኢሰመኮ ጠይቋል፡፡

ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ “የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችንና አባላትን፣ የሚዲያ አባላትንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ዒላማ ያደረገ እስር እና ወከባ በእጅጉ አሳስቦኛል” ብሏል፡፡

በዚህ ወር ውስጥ ብቻ በርካታ የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን አዘጋጆችና አክቲቪስቶች መታሰራቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ይኸውም ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝና የሚዲያ አዋጁን በሚጻረር መልኩ የተፈጸመ ስለመሆኑ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

ኢሰመኮ በዚህ ወር የታሰሩ ካላቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መካከል፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነውና በአሁኑ ወቅት አራት ኪሎ ሚዲያ የተሰኘ ዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስርቶ በአዘጋጅነት የሚሰራው ዳዊት በጋሻው፣ የኢትዮ ሰላም ዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን አዘጋጅ ቴዎድሮስ አስፋው፣ ለ የኔታ ቲዩብ የምትሠራው ገነት አስማማው፣ የሮሃ ኒውስ አዘጋጅ አራጋው ሲሳይ፣ የአማራ ድምፅ አዘጋጅ ጌትነት አሻግሬ፣ የጉራጌ ሚዲያ ኔትወርክ አዘጋጅ በየነ ወልዴ፣ ለአሻራ ሚዲያ የምትሠራው ሰናይት አያሌው፣ የ ኢ ኤም ኤስ አዘጋጅ ሳሙኤል አሰፋ እንዲሁም በማኅበረሰብ አንቂነት እና በሚዲያ ሥራም የምትታወቀው የ ኢትዮ ንቃት አዘጋጇ መስከረም አበራ እንደሚገኙበት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

በእስር ላይ ከሚገኙት የሚዲያ ባለሙያዎች ውስጥ ከፊሎች በእስር ወቅት “ተገቢ ላልሆነ አያያዝ” መዳረጋቸውንና ከፊሎች ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ እስር ተዳርገው እንደነበሩ የገለጸው ኢሰመኮ፣ ሌሎቹ ደግሞ “ከተለያየ ጊዜ መጠን እስር በኋላ የተለቀቁ ናቸው” ሲል አመልቷል፡፡

ኢሰመኮ በዝርዝር ካስቀመጣቸው የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ እና ከዚያም ቀደም ብሎ ፍርድ ቤት ቀርበው፣ የ13 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶባቸዋል፡፡

ፖሊስ ኹሉንም ታሳሪዎች፣ “ሁከት እና ብጥብጥ በማሥነሳት ወንጀል” እንደጠረጠራቸው ለፍርድ ቤት ያሳወቀ ሲኾን፣ በተጨማሪም መስከረም አበራ፣ ለ “ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወታደራዊ ሥልጠና እና የተኩስ ልምምድ ስትሰጥ ነበር፤” ማለቱ ይታወሳል፡፡

ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው፣ በተራዘመ ቅድመ-ክስ እስር ወይም ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን፣ የተወሰኑት ደግሞ በነጻ ወይም በዋስትና መለቀቃቸውን ስለማረጋገጡም ጠቅሷል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 (የሚዲያ አዋጅ)፣ በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፣ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ፣ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ-ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑ በግልጽ እንደሚደነግግ ያስታወቀው ኢሰመኮ፣ “በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ” ሲል አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል፣ እናት ፓርቲን፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን እና ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲን ጨምሮ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ያተኮሩ እስሮች እና ወከባዎች እየተፈጸሙ እንደሚገኙ ኢሰመኮ አስታውሷል፡፡

“መንግሥት የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚያተኩር እስር ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብቶች ላይ የሚያስፈራራ፣ የሚያሸማቅቅ እና የሚገድብ ውጤት እንዳይኖረው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ነው” በማለት አስጠንቅቋል፡፡

በመሆኑም የመንግሥት የጸጥታ አካላት በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና በማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ካተኮረ እስርና ማዋከብ እንዲቆጠቡ፣ በወንጀል የተጠረጠሩና በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በቅድመ-ክስ ሊታሰሩ የሚገባቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሁኔታም በሕግ በተመለከተው መንገድ ብቻ በጥብቅ ጥንቃቄ አንዲፈጸምና የተጠረጠሩ ሰዎችን ሁሉ ከምርመራ በፊት ከማሰር እንዲቆጠቡም ጠይቋል፡፡

XS
SM
MD
LG