በኢኮኖሚ ፍልጎቶች ምክንያት ግብፅ በተናጠል ከሊቢያ ጋር የምትጋራውን የባህር አዋሳኝ ድንበር ባለፈው ሳምንት ለመከለል መወሰኗ፣ ሰፊ የባህር ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ሀብቶችን እና በግብፅ እና ሊቢያ የባህር ዳርቻዎች ዋሃ ውስጥ ሰርስሮ የማውጣት መብት በቀጠና መንግስታት መካከል መወነጃጀል አስነስቷል።
የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ሀገራቸው ከሊቢያ ጋር የምትጋራውን የባህር ድንበር ማካለል መወሰናቸው፣ በፓርላማው ከሚደገፈው የሊቢያ ተቀናቃኝ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር በተጨማሪ፣ መቀመጫውን በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ ያደረገው የብሄራዊ አንድነት መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተቃውሞ ገጥሞታል።
የአንድነት መንግስቱ አጋር የሆነችው ቱርክ ግጭቱን ለመፍታት ሁለቱም ሀገራት በባህርዳር ድንበር ስምምነት ዙሪያ እንዲደራደሩ እሁድ እለት ጥሪ ማቅረቧ ተዘግቧል።
የግብፅ የፖለቲካ እና ሶሲዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ሳይድ ሳዴቅ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት ግብፅ ድንበሯን በማካለል ትክክለኛ ውሳኔ መወሰኗ ግልፅ ባይሆንም አስፈላጊ የኢኮኖሚ ፍላጎቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸው እና ካይሮ ሊቢያ እንደገና የተረጋጋች ሀገር እስክትሆን መጠበቅ እንደማትችል ገልፀዋል።
"ሊቢያ ከቀድሞው መሪ ሙአማር ጋዳፊ ውድቀት ወዲህ በጣም የተከፋፈለች ሀገር መሆኗን እና መቼ ምርጫ እንደሚካሄድ እና መቼ መረጋጋት መረጋጋት እንደሚኖር ስምምነት ያለመኖሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አሁን ሁሉም ሀገሮች የየራሳቸውን ጥቅም ማስጠበቅ ያለባቸው ይመስለኛል። ሌሎች ያሉበትን ሁኔታ እስኪያስተአካክሉ ድረስ ግብፅ የራሷን የተፈጥሮ ኃብቶች አለመጠቀም አትችልም።"
በሊቢያ እ.አ.አ በታህሳስ 2021 ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም በመደረጉ፣ በተቀናቃኝ ሊቢያኖች እና ዓለም አቀፍ ፓርቲዎች በሚደገፉ ሁለት መንግስታት ሀገሪቱ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ውስጥ ወድቃለች።
በፓሪስ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ መምህር የሆኑት ካታር አቡ ዲያብ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት "በምስራቅ ሜዲትራኒያን ውስጥ የሚገኘው ሰፊ የባህር ውስጥ ጋዝ ሀብቶች" ግብፅን መቀመጫውን ትሪፖሊ ካደረገው የሊቢያ መንግስት እና ድጋፍ ከምትሰጠው ቱርክ ጋር ግጭት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
"ምንም እንኳን ቱርክ ለሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን በምታደርገው ድጋፍ ከአንካራ ጋር የቀጠለ የፖለቲካ ግጭት ቢኖራትም፣ ቱርክ ድጋፍ የምትሰጠው በአብዱል ሃሚድ ዴቢህ የሚመራው የትሪፖሊ የሊቢያ መንግስት የባህር ጉዳይን በግብፅ ላይ እንደማነቆ እየተጠቀመበት ቢሆንም፣ እና ለመንግስቱ እውቅና ባትሰጠውም፣ ግብፅ ቱርክን ላለማስቆጣት ለአመታት ስትጠነቀቅ ቆይታለች። "
አቡ ዲአብ አክለው "ግብፅ እና ቱርክ በሊቢያ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ስልታዊ ፍላጎት ያላቸው እንደመሆኑ፣ በቀጣዩ አመት በሁለቱ ሀገራት መካከል ድርድሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይችላሉ" ሲሉ ይከራከራሉ።
አትላንቲክ ካውንስል በተሰኘ ተቋም፣ መቀመጫቸው በዋሽንግተን ዲሲ የሆነው የፖለቲካ እና ኃይል ተንታኝ ፓውል ሱሊቫን "በምስራቅ ሜዲትራኒያን ያለውን ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት" ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀጠናው ያሉ ሁሉም ሀገሮች የይገባኛል ጥያቄ እያነሱ በመሆኑ የሆነ አይነት አጠቃላይ ስምምነት ላይ እስከሚደረስ ደረስ ውጥረት እየጨመረ መሄዱ የማይቀር ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።