ግብጽ የአየር ንብረት ጉባዔው በሚካሄድበት ወቅት ሰላማዊ ሰልፍ እንዲካሄድ ጥሪ ያቀረቡ ብዙ ሰዎችን በጉባኤው ዋዜማ አስራለች ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች ተናገረ።
የሰብዐዊ መብት ቡድኑ ይህን ያለው ትናንት ዕሁድ ባወጣው መግለጫ ነው። ጉባዔው የሚካሄድባት የመዝናኛ ከተማ ሻርም ኤል ሼኽ ጥብቅ የጸጥታ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑ ተመልክቷል።
የከተማዋ ታክሲዎች በሙሉ ካሜራ እንዲያስገጥሙ በመንግሥቱ ባለስልጣናት መታዘዛቸውን የገለጠው ቡድኑ ዐላማው የደህንነት ኅይሉ አሽከርካሪዎቹንም ተሳፋሪውንም ለመከታተል እንዲችል ነው ብሏል።
የግብጽ ባለስልጣናት በተጨማሪም "ወደጉባዔው ስፍራ መግቢያ ፈቃድ ለማግኘት የሚያስፈልገውን ምዝገባ አላስፈላጊ በሆነ መንገድ አወሳስበውታል" ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች አመልክቷል።
ካሁን በፊት በነበሩት ጉባዔዎች ወቅት የጉባዔው ስፍራ ግሪን ዞን ክፍት እንደነበር እና በአየር ንብረት ጉዳዮች ሃሳብ ለመለዋወጥ እንዲሁም ተሳታፊዎቹ ከህዝቡ ጋር እንዲገናኙ ዕድል ሰጥቶ እንደነበር ሂዩማን ራይትስ ዋች አስታውሷል።
ከዚህም ሌላ የግብጽ መንግሥት ለጉባዔው ተሳታፊዎች በስልካቸው ላይ የፓስፖርት ቁጥራቸውን ጨምሮ የግል መረጃ በመስጠት የሚሞሉት ማመልከቻ ማውጣቱን የጠቀሰው የሰብዐዊ መብት ድርጅቱ ሁለት የሀገር ውስጥ የመብት ድርጅቶች ማመልከቻውን በተመለከተ ባካሂዱት ግምገማ የማመልከቻው መተግበሪያ የስልኩን ካሜራ እና የቦታ ጠቋሚ እንዲሁም የብሉቱዝ መገናኛ የሚጠይቅ መሆኑን አይተዋል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዋች።
በእጅ ስልክ ላይ የሚሞላው ማመልከቻ ለሶስተኛ አካል ሊተላለፍ እንደሚችል እና የግል መረጃ ደህንነት እንደሚደቅን አክሎ ጠቁሟል።