በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በግብጽ ሻርም ኤል ሼኽ


የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በግብጽ ሻርም ኤል ሼኽ
የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በግብጽ ሻርም ኤል ሼኽ

ግብጽ ሻርም ኤል ሼኽ ላይ በተከፈተው የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ የተገኙት የዓለም መሪዎች የበካይ ጋዝ ልቀትን በይበልጥ እንዲቀንሱ እና በእየር ግለት ምክንያት ለተጎዱ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ብርቱ ግፊቱ በርትቶባቸዋል።

ቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘው የግብጿ የመዝናኛ ከተማ የተመዱ ጉባዔ ኮፕ-27 የተከፈተው በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ሀገሮች በዚህ ዓመት ብቻ የብዙ ሺህ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉትን እና በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ ውድመቶችን ያስከተሉ የመሳሰሉ ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች እየጨመሩ ባሉበት በዚህ ወቅት ነው።

ሩስያ በዩክሬን ላይ ከምታካሂደው ጦርነት እና ከኃይል ምንጭ ችግሮች እንዲሁም ከዋጋ መናር እና በኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የተያያዙ የምጣኔ ሀብት ቀውሶች ቢኖሩም መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥን መታገላቸውን እንዲቀጥሉ የጉባዔው መሪዎች ትናንት ዕሁድ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ጥሪ አቅርበውላቸዋል።

የዓለም አየር ሙቀት በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ ከነበረበት መጠን ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሲየስ በላይ እንዳያልፍ ለማድረግ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ባለው ጊዜ የበካይ ጋዞች ልቀት በ45 ከመቶ መቀነስ ይኖርበታል።

ይሁን እንጂ አሁን ባለው አካሄድ በ2030 የከባቢ አየር የካርቦን ብክለት መጠን በ10 ከመቶ እንደሚጨምር እና የምድራችን ሙቀት መጠን በ2 ነጥብ 8 ሲልሲየስ እንደሚጨምር በቅርብ ቀናት የወጡ አዲስ ጥናቶች አመልክተዋል።

ከ194 ሀገሮች መካከል 29ኙ ብቻ ባለፈው ዓመት ግላስጎ ላይ በተካሄደው የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ በቀረበው ጥሪ መሰረት የተሻሻለ ዕቅድ ማቅረባቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ባለሥልጣን ሳይመን ስቲል ተናግረዋል።

በሁለቱ ቀናት ንግግር 110 የሚሆኑ የሀገሮች መሪዎች የሚካፈሉ ሲሆን ዋናዋ የበካይ ጋዝ አመንጪ የሆነችው የቻይና መሪ ዢ ጂንፒንግ አይገኙም።

የሁለተኛዋ የበካይ ጋዝ አመንጪ ሀገር የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የነገው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ላይ ጉባዔተኞቹን እንደሚቀላቀሉ ታውቋል።

XS
SM
MD
LG