በዓለማችን ከፍተኛ ነዋይ በሚፈስበት የፋሽን ኢንዱስትሪ ተቀባይነት አግኝተው የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳትን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከቻሉ ኢትዮጵያዊ የፋሽን ዲዛይነሮች መካከል ገነት ከበደ በዋናነት ትጠቀሳለች። ገነት ፓራዳይዝ ፋሽን የተሰኘ ድርጅት መስርታ ባህላዊውን የሽመና ውጤት በዘመናዊ መልክ ማቅረብ ከጀመረች 30 አመታት ያስቆጠረች ሲሆን ስራዎቿን እና በዘርፉ ያበረከተችውን አስተዋፅኦ የሚዘክር ታላቅ የፋሽንና የሙዚቃ ትርዒት ለማካሄድ ዝግጅት ተጀምሯል።
ኢትዮጵያዊቷ እውቅ ዲዛይነር ገነት ከበደ የፋሽን ጥበብን በጣሊያን እና አርጀንቲና ተምራ ወደ ሀገሯ ትመለስ እንጂ፣ ለፋሽን እና ለዲዛይን ጥበብ ያላት ፍቅር የሚጀምረው ግን ገና ከልጅነቷ ነው።
ገነት ከ30 ዓመት በፊት የዲዛይኒንግ ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ በከፈተችው ፓራዳይዝ ፋሽን ድርጅት አማካኝነት የኢትዮጵያ አልባሳትን በዘመናዊ መልክ እየሰራች ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ጀመረች። በተለይ የምትታወቅበት ደግሞ በባህላዊ የሽመና ውጤቶች ዘመናዊ የሙሽራ እና የሚዜ አልባሳትን በመስራት ነው።
በሀገር ደረጃ በዘርፉ የካበተ ልምድ በሌለበትና እንደ ዋና ስራ ወይም መተዳደሪያ የመሆኑ እድል አነስተኛ በሆነበት የፋሽን ኢንዱስትሪ ስራዎቿን ማውጣት የቻለችው ገነት ታዲያ በዓለም ገበያ ውስጥም ተፅዕኖ መፍጠር ችላለች። ገነት ፋሽን በሚል ስያሜ የሚታወቁ የተለያዩ በባህላዊ ጨርቆች የተሰሩ አልባሳትንም ለገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።
ይህንን የገነት የ30 አመት የፋሽን ዲዛይን ሙያ ለመዘከር ታዲያ ከአዲስ አበባ ፍሬንድ ሺፕ ፓርክ በቴሌቭዥን በቀጥታ ለዓለም የሚሰራጭ ታላቅ የፋሽን ትርዒት ለማካሄድ ዝግጅት ተጀምሯል። የፕሮግራሙ ፕሮዲዩሰር እና በኢትዮጵያ ዙሪያ ከ24 በላይ ዶክመንተሪዎችን የሰራው አንቷን ሊንድሌይ እንደሚለው የፋሽን ትርዒቱን የምትመራው የገነት የረጅም ግዜ ጓደኛ እና ታዋቂዋ ኢትዮጵያዊት ሞዴል ሊያ ከበደ ናት።
በዝግጅቱ ላይ 'ገነት ዲዛይን' በሚል አዲስ ስያሜ የሚተዋወቁ አዳዲስ የገነት ልብሶች ለዕይታ የሚቀርቡ ሲሆን የገነትን የ30 አመት የሚያስቃኝ ሌላ የጥቁር እና ነጭ የፎቶ ዓውደ ርዕይ እንደሚኖርም አንቷን ያስረዳል።
የገነት የ30 አመት የፋሽን ዲዛይን ጉዞ ሲከበር ታዲያ ገነት ለአዲስ ስራዎችም እየተዘጋጀች ነው። በተለይ ገና ብዙ ይቀረዋል የምትለው የሽመና ጨርቆች በዘመናዊ መልክ በስፋት እንዲመረቱ እና ለገበያ እንዲቀርቡ ማድረግ እና ሙያዋን ለወጣቶች የምታካፍልበት ትምህርት ቤት መክፈት ህልሟ ነው። ሙያዋን ከሚዘክረው የፋሽን ትርዒት የሚሰበሰበው ገቢም በካንሰር በሽታ ለተጠቁ ህፃናት ህክምና እንደሚውል አዘጋጆቹ ገልፀዋል።