የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ ዛሬ ሐሙስ ጠዋት በስልክ ተነጋግረዋል። የሁለቱ መሪዎች ውይይት ኢኮኖሚን፥ ከታይዋን ጉዳይ በተያያዘ ያሉትን ውጥረቶች እና ሩሲያ ዩክሬን ላይ እያካሄደች ያለውን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ከንግግሩ ቀደም ብሎ ዋይት ኃውስ የሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
ትናንት ረቡዕ የዩናይትድ ስቴትስ የብሄራዊ ጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ በሰጡት ቃል፣
"ፕሬዚዳንት ባይደን ከፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ ጋር ያለው ግንኙነት መስመር ክፍት ሆኖ እንዲቆይ ይፈልጋሉ። ክፍት ሆኖ መቆየት ስላለበት ነው። ከቻይና በትብብር ልንሰራ የምንችልባቸው ጉዳዮች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የፍትጊያ እና ውጥረት መንስዔ የሆኑ ጉዳዮችም መኖራቸው ግልጽ ነው" በማለት አስረድተዋል።
የደቡብ ቻይና ባህርን የሚመለከተው ጉዳይ እና ቃል አቀባዩ 'ቻይና በአካባቢው ሀገሮች ላይ የምታሳየው የጨቋኝ እና የጠብ አጫሪነት ባህሪ ሲሉ በገለጹት ሳቢያ ያሉት ውጥረቶች በመሪዎቹ ንግግር እንደሚነሱም ነበር ያስታወቁት።
ፕሬዚዳንት ባይደን እና ፕሬዚዳንት ሺ ጂፒንግ የስልክ ውይይታቸውን ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፐሎሲ ታይዋንን ማቀዳቸውን ተከትሎ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የኃይል ምላሽ እንሰጣለን" የሚል ማስጠንቀቂያ ባሰሙበት በዚህ ወቅት መሆኑ ነው።
ጃን ከርቢ በትናንቱ ገለጻቸው "በዲፕሎማሲ ረገድ ለታይፔይ ሳይሆን ለቤጂንግ ዕውቅና የሚሰጠው የዩናይትድ ስቴትስ ፖሊሲ አልተለወጠም" ብለዋል።