በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፍ/ቤት የመስከረም አበራን ዋስትና ሲያፀና ተመስገን ደሳለኝ ላይ ክስ እንዲመሰረት አዘዘ


የገበያኑ ዩቲዩብ ሚዲያ መስራችና አዘጋጅ ሰለሞን ሹምዬ፣ የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ፣ የሮሃ ዩቲዩብ ሚዲያ አዘጋጇ መዓዛ መሐመድ፣ “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ ዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ መስከረም አበራ
የገበያኑ ዩቲዩብ ሚዲያ መስራችና አዘጋጅ ሰለሞን ሹምዬ፣ የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ፣ የሮሃ ዩቲዩብ ሚዲያ አዘጋጇ መዓዛ መሐመድ፣ “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ ዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ መስከረም አበራ

“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ ዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ መስከረም አበራ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንድትፈታ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፣ ትናንት ሰኔ 6/2014 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ እንዲፀና የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ የስር ፍርድ ቤት የተሰጠው የዋስትና መብት እንዲሻር መርማሪ ፖሊስ ትናንት ያቀረበውን ይግባኝ አዳምጦ፣ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ የፖሊስን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል፡፡

በዚህም ፍርድ ቤቱ “መስከረም በ30 ሺህ ብር ዋስ ከእስር ትለቀቅ” በሚል የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ እንዳጸና ጠበቃዋ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡

መስከረምን ለማስፈታት የተወሰነውን የዋስትና ገንዘብ እንዳስያዙም አቶ ሄኖክ ጨምረው ገልፀዋል። ይሁን እንጂ “ጉዳዩን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት እወስደዋለሁ በሚል ፖሊስ አልለቀቃትም” ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ከሳምንት በፊት የዋስትና መብታቸው ተሽሮ መዝገባቸው ወደ ፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተመለሰው የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ፣ የገበያኑ ዩቲዩብ ሚዲያ መስራችና አዘጋጅ ሰለሞን ሹምዬ እና የሮሃ ዩቲዩብ ሚዲያ አዘጋጇ መዓዛ መሐመድም ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዛሬ ችሎቱ፣ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርት የ15 ቀናት ጊዜ ሰጥቶታል።

ፖሊስ በተመስገን ላይ የሚያደርገውን ምርመራ አጠናቆ ጉዳዩን ለዐቃቤ ሕግ ማስተላለፉን ለፍርድ ቤት የገለጸ ሲሆን፣ መዝገቡ እንደደረሰው የገለጸው ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ “ተደራራቢ ወንጀል ፈጽመዋል ብዬ ስለጠረጠርኳቸው ክስ ለመመስረት የ15 ቀናት ጊዜ ይሰጠኝ” ሲል መጠየቁን የተመስገን ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ገልጸዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ “ከመጀመሪያ ጀምሮ ያለውን የምርመራ ሂደት የሚያውቅ በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም” በማለት መከራከራቸውንም የተናገሩት አቶ ሄኖክ፣ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ዐቃቤ ሕግ የጠየቀውን ጊዜ መፍቀዱን አመልክተዋል፡፡

የገበያኑ ዩቲዩብ ሚዲያ መስራችና አዘጋጅ ሰለሞን ሹምዬ፣ እንዲሁም የሮሃ ዩቲዩብ ሚዲያ አዘጋጇ መዓዛ መሐመድን በተመለከተ ደግሞ፣ ፖሊስ በሁለቱ የሚዲያ ባለሞያዎች ላይ የሚያደርገውን ምርመራ አለማጠናቀቁን ገልጾ ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ዛሬን ጨምሮ ስድስት የምርመራ ቀናትን በመፍቀድ፣ ለሰኔ 13/2014 ዓ.ም ቀጠሮ እንደሰጠ ነው አቶ ሄኖክ ገልፀዋል።

XS
SM
MD
LG