- በያየሰው ሽመልስ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ
በመስከረም አበራ የዋስትና መብት ላይ የፖሊስን ይግባኝ ያዳመጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ሰጠ። በያየሰው ሽመልስ ላይ ደግሞ የሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ የተፈቀደ ሲሆን፣ ጠበቃው ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል።
ዛሬ ሰኞ ሰኔ 6/2014 ዓ.ም ጠዋት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረበችው፣ “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ መስከረም አበራ፤ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንድትለቀቅ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ይግባኝ አቅርቦባታል፡፡
በዛሬ ችሎቱ የመርማሪ ፖሊስን እና የጠበቃዋን ክርክር ያዳመጠው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ የስር ፍርድ ቤት፣ ምርመራውን አለማጠናቀቁን በመግለጽ ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ያቀረበውን ጥያቄ ባለመቀበል ነበር በ30 ሺህ ብር ዋስ እንድትፈታ ትዕዛዝ የሰጠው፡፡
ይሁን እንጂ የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም፣ ፖሊስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኙን አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ይግባኝ ከሰዓት ከ8፡30 ጀምሮ መመልከቱን የገለጹት የመስከረም ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ፣ ዋስትናዋ እንዲሻር ፖሊስ በምክንያትነት ያቀረበው “የሚቀሩኝ የምርመራ ስራዎች አሉኝ” የሚል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እርሳቸው በበኩላቸው “ከዚህ ቀደም ለፖሊስ በቂ የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶታል፤ በቤቷ የተገኙ መፅሐፍትን ለመመርመር ደግሞ ዋስትናዋ እንዲሻር ይግባኝ መጠየቅ ተገቢነት የለውም” በማለት የፖሊስን ይግባኝ ተቃውመው ክርክር ማቅረባቸውን ለቪኦኤ አብራርተዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱም ለውሳኔ ለነገ ሰኔ 7/2014 ዓ.ም መቅጠሩን ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና “የኢትዮ ፎረም” አዘጋጅ በነበረው ያየሰው ሽመልስ ላይ ደግሞ ለፖሊስ የ7 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን፣ ጠበቃው ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቁ ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ የያየሰውን ጉዳይ ሲያዳምጥ፣ ፖሊስ “በባንክ ቁጥሩ የ18 ሚሊዮን ብር እንቅስቃሴ አግኝቻለሁ፤ በምርመራዬ ለማጠናቅቃቸው ጉዳዮች የ14 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ” ሲል ጥያቄ ማቅረቡን ጠበቃው አቶ ታደለ ገብረመድህን ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡
ደምበኛቸው የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ አንቀሳቅሶ እንደማያውቅ በመግለጽ መከራከራቸውንም የገለጹት አቶ ታደለ፣ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ተጨማሪ 7 የምርመራ ቀናትን እንደፈቀደ ነው ያብራሩት፡፡
ይሁን እንጂ የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም በነገው ዕለት ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን አቶ ታደለ አመልከተዋል፡፡
የ”ኢትዮ ንቃት” ዩቲዩብ ሚዲያ መስራች እና አዘጋጅ መስከረም አበራ ከግንቦት 13/ 2014 ዓ.ም ጀምሮ፣ የ”ኢትዮ ፎረም” አዘጋጅ የነበረው ያየሰው ሽመልስ ደግሞ ከግንቦት 18/2014 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ ሁለቱም “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት” ወንጀል ተጠርጥረው ነው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡