በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን የስዊድንና የፊንላንድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ይደግፋሉ


ባይደን የስዊድንና የፊንላንድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ይደግፋሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:49 0:00

ባይደን የስዊድንና የፊንላንድን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ይደግፋሉ

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትናንት ሀሙስ ስዊድንና ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል ያቀረቡትን ጥያቄ ላቀ ባለ የደስታ ስሜት ተቀብለውታል፡፡ ዘመናዊ ጦር ያላቸው ሁለቱ የአውሮፓ አገሮች፣ ፊንላንድና ስዊድን፣ የኔቶ የደህንነት ህብረትን፣ ወደ ሰሜን ምዕራብ የሩሲያ ድንበር ለማስፋት እንደሚረዱት ተነግሯል፡፡

ከስዊድንና የፊንድላንድ መሪዎች ጋር ትናንት ሀሙስ በዋይት ሀውስ የተገናኙት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የኔቶ አባል አገራት፣ ሁለቱን አገሮች ወዲያኑ ወደ ህብረቱ ለመቀበል የሚያበቃቸው በርካታ ምክንያቶች አሏቸው ብለዋል፡፡

ባይደን “ስዊድንና ፊንላንድ ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቀሟት፣ ጠንካራ ጦር እና የጠነከረና ግልጽነት ያለው የምጣኔ ሀብት አላቸው፡፡ ትክክለኛ ስለሆነው ነገርም ጠንካራ የሞራል ጽንሰ ሀሳብ አላቸው፡፡ እያንዳንዱን የኔቶ መስፈርት ያሟላሉ፡፡” በማለትም መስክረውላቸዋል፡፡

የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር መግደሌና አንደርሰን፣ አገራቸው የሶቭየት ህብረትን ተስፋፊነት ለመዋጋት፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ወደ ተቋቋመውና፣ 30 አባላት ወዳሉት ወታዳራዊ የመከላከያ ጥምረት፣ ብዙ ጥቅሞችን ይዛ እንደምትመጣ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በስፍራው ባሰሙት ንግግር “የጋራ እሴቶቻችንና እምነቶቻችን ዴሞክራሲና ነጻነት ሲሆኑ አሁን ለፈተና የቀረቡ እሴቶቻችንና እምነቶቻችን ናቸው፡፡ ዛሬ በዩክሬን ያለው ሁኔታ በአውሮፓ ታሪክ የነበሩትን የጨለማ ቀናት ያስታውሱናል፡፡ በእነዚያ የጨለማ ቀናት በቅርብ ወዳጆች መካክል መሆን ታላቅ ነገር መሆኑን መናገር ይኖርብኛል፡፡” ብለዋል፡፡

ይሁን እንጅ አንዳንድ ተንታኞች ይህ እርምጃ ሩሲያን የበለጠ ሊያስቆጣ ይችላል ይላሉ፡፡ ከብሩክኒግስ ተቋም ሚላኔ ሲሶን “የኔቶ ወደ ፊንላንድና ስዊድን መስፋፋ ቆስቋሽነት ይመስለኛል፡፡ እነሱን በህብረቱ ውስጥ መጨመር ስለሚሰጠው ዋጋ ማንም ሰው የፈለገውን ሊል ቢችልም አሁን ላለው ጉዳይ የሚሰራ ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንዲያውም የስትራቴጂ ትዕግስት ማጣት መኖሩን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ኔቶ ወደ ምስራቅ የሚያደርገው መስፋፋት ለሩሲያ ስጋት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ዩክሬን ህብረቱን ለመቀላቀል ያላት ፍላጎት በየካቲት ለጀመሩት የዩክሬን ወረራቸው ምክንያት እንደሆናቸውም ተናግረዋል፡፡

“የኔቶ መስፋፋት - ይህ ፍፁም ሆን ተብሎ ለዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖሊሲ ፍላጎት ሲባል የተፈጠረ ሰው ሰራሽ ነገር ነው፡፡ በአጠቃላይ ኔቶ የአንድ አገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሳሪያ እየሆነ ነው፡፡” ሲሉም ፑቲን ስለ ህብረቱ ያላቸውን አስተያየት ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳን ባይደን ለምክር ቤቱ ያቀረቡትን ጥያቄ እንደሚያጽድቀው እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኔቶ አባል የሆነቸው ቱርክ መሰናክል ሆናለች፡፡ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሰፕ ጣይብ ኤርዶጋን አመልካቾቹ አገሮች ለአሸባሪዎቹ መናኻሪያ ገነት ሲሆኑ በቱርክም ላይ ማዕቀብ መጣላቸውን ይገልጻሉ፡፡

“የቱርኩ ፕሬዚዳንት ጉዳዩን አሰመልክቶ በሰጡት መግለጫ “30 የሚሆኑ አሸባሪዎች ተላልፈ እንዲሰጡ ጠይቀን ነበር፡፡ እነሱ (ስዊድኖች) ግን ይህን አናደርግም አሉ፡፡ አሸባሪዎቹን ለኛ አሳልፋችሁ አትሰጡንም የኔቶ አባል ለመሆን እንድፈቅድላችሁ ግን ትጠይቁናላችሁ፡? ኔቶ የደህንነት አካል ነው፡፡ የደህንነት ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ አዎ የዚህን የደህንነት ተቋም ደህንነት ለማሳጣት አዎ ልንል አንችልም፡፡” ብለዋል፡፡

የፊንላንድ ፕሬዚዳንት ሳውሊ ኒስቶ፣ አገራቸው የአንካራን መንግሥት ማነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም “እንደ ኔቶ አጋርነታችን ቱርክ የኛን ደህንነት ለመጠበቅ እንደምትሰራ ሁሉ እኛም የቱርክን ደህንት እንጠብቃለን፡፡ ሽብርተኝነት ላይ የጸና አቋም አለን፡፡ ሽብርተኝነትን በየትኛውም መልኩ እናወግዛለን፡፡ ሽብርተኝነትንም ለመዋጋት ተግተን እንሰራለን፡፡” ብለዋል፡፡

በኔቶ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የነበሩ ኩርት ቮልከር ሌሎች ተጨማሪ አገሮች ሳይቀሩ በቅርቡ የኔቶ አባል ለመሆን ይጠይቃሉ ሲሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ አያይዘውም “ጠንካራ ዴሞክራሲ፣ የአውሮፓ ህብረት አባል እና እንዲሁም ጠንካራ ጦር ያላቸው ፊላንድና ስዊድን፣ ከኔቶ አባል ውጭ ሆነው ደህንነት የማይሰማቸው ከሆነ፣ ይህ በግልጽ፣ እሰከዛሬ ድረስ የተገለሉ አገሮች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ አሁንም ቢሆን ግሬይ ዞን ካንትሪስ ተብለው የተቀመጡ እነ ዩክሬን፣ ጆርጂያ፣ ሞልዶቫ እና አንዳንዶቹ የባልካን አገሮች ራሳቸው ከኔቶ ውጭ ደህንነት ሊሰማቸው አይችልም፡፡ ስለዚህ ይህ ያንን ፍላጎት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡” ብለዋል፡፡

ትናንት ሀሙስ ረፋዱ ላይ ባይደን በፕሬዚዳንትነታቸው ወደ እስያ የመጀመሪያቸው የሆነውን ጉዞአቸውን ጀምረዋል፡፡ በቅድሚያ የዩናይትድ ስቴትስ አጋር የሆኑትን የደቡብ ኮሪያና የጃፓን መሪዎችን የሚያነጋገሩ ሲሆን፣ “ኳድ 4” በተባለው የአራቱ አገሮች ጉባኤ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ የስብሰባዎቹ ትኩረት በአብዛኛው በዩክሬን ጉዳይ ላይ እንደሚሆንም ተገምቷል፡፡

XS
SM
MD
LG