በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩክሬን ጉዳይ የአፍሪካ ሃገሮች እንዲናገሩ ተጠየቁ


በዩክሬን ጉዳይ የአፍሪካ ሃገሮች እንዲናገሩ ተጠየቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:48 0:00

በዩክሬን ጉዳይ የአፍሪካ ሃገሮች እንዲናገሩ ተጠየቁ

“ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሰነዘረቸውን ወረራ በመቃወም ድምፃቸውን የሚያስሙ ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች ያስፈልጋሉ” ሲል የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ጥሪ አድርጓል።

ዩክሬንን በመውረር ተጠያቂ የሆነችውን ሩሲያን በማውገዝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በዚህ ሳምንት ያሳላፈውን ውሳኔ ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች መደገፋቸው ተዘግቧል።

ባለሙያዎች ግን የአፍሪካ ሃገሮች የዩክሬንን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት መጠበቅን በሚመለከት የሚናገሩት ጥቂት መሆኑን ይናገራሉ።

ዩናይትድ ስቴት የአፍሪካ አገሮች ሩሲያ በአጎራባቿ ዩክሬን ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት አስመልክቶ የበለጠ እንዲናገሩ እንደምትፈልግ ሐሙስ ዕለት የአፍሪካ ጋዜጠኞችን በድረ ገጽ ያነጋገሩት የዩናይትድ ስቴትስ ረዳት የአፍሪካ ጉዳዮች ጸሀፊ ሞሊ ፊ ዩክሬን ገልፀዋል።

“ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ድምጽ በዓለም ማህበረሰብ ውስጥ ዋጋ ያለው ስለመሆኑ ጠንካራ እምነት አላት፡፡ ስለዚህ በዓለም ንግግር ውስጥ ድማችሁ ዋጋ አለው፡፡" ያሉት ሞሊ "ጠቅላላው የዓለም ማኅበረሰብ ይህንን ጠበኝነት ተቃውሞ በአንድ ድምጽ በተናገረበት ፣ ዘመን የማይሽረው መርህን በደገፈበት ጊዜ የናንተ ድምጽ እጅግ ወሳኝ መሆኑን እናምናለን፡፡ ይህ መርህ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን እና የሰላማዊ ዜጎች ደህንነት መጠበቅን ይጨምራል፡፡” ብለዋል።

ሰዎች በሞተር ብስክሌት በናይጄሪያ አቡጃ ከተማ ዩክሬን ኤምባሲ ፊት ለፊት ሲያልፉ እኤአ የካቲት 25 2022
ሰዎች በሞተር ብስክሌት በናይጄሪያ አቡጃ ከተማ ዩክሬን ኤምባሲ ፊት ለፊት ሲያልፉ እኤአ የካቲት 25 2022

ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው የተባበሩ መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ 141 አገሮች ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ አውግዘዋል፡፡

ከአፍሪካ አገሮች ውሳኔውን በመቃወም ድምጽ የሰጠችው ኤርትራ ብቻ ናት፡፡

ሌሎች 16 የሚሆኑን የአፍሪካ አገሮች ድምጽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

በመከሬራ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ካሲጃ አፑሊ አፍሪካ የራሷ የሆነ ብዙ የውስጥ ችግሮች ስላሉባት እንዲህ ያሉ ነገሮች ውስጥ እጇን አትከትም ብለዋል፡፡

ይህኑን ሲገልጹም “እኛ ሁልጊዜ የራሳችን ችግሮች አሉብን፡፡ እውነት ነው ይህ ጉዳይ የዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ስለሚነካ ይመለከተናል ግን እዚህ ውስጥ ገብተን መሳተፍ ያለብን አይመስለኝም፡፡ አፍሪካ በ እንዲህ ያሉ ነገሮች ውስጥ በመግባት ለራሷ የሚጠቅማትን ነገር መቅረጽ የምትችል አይመስለኝም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጉዳዩ እየተካሄደ ባለበት አውሮፓ ውስጥ ጉዳዩን በመከታተል ላይ የሚገኝ የአውሮፓ ህብረት አለን፡፡ የአፍሪካ ህብረት በዚህ ጉዳይ እጁን መክተቱን ተቀባይነት ያለው አይመስለኝም፡፡” ብለዋል፡፡

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃቱን የጀመረቸው ባለፈው ሳምንት ነው፡፡ ድርጊቱን ዓለም ያወገዘው ሲሆን ኃይሏን ከዩክሬን እንድታስወጣም ጠይቋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ አገሮች ሩሲያን በምጣኔ ሀብት ማእቀብ ደብድበዋል፡፡

ዋሌ ኦሎሶላ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ባለሙያ ናቸው፡፡ አፍሪካ በዚህ ግጭት ወገናዊ አቋም አትወስድም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአገሮችን መብት ለሚጠብቀውና ለሚያከብረው ዓለም አቀፍ ህግ ልትቆም ይገባታል በማለትም ተናግረዋል፡፡

ይህን ሐሳባቸውን ሲያብራሩም “ የውይይቱን አቅጣጫ በመቅረጽና በመወሰን፣ አሁን ያለው አለም አቀፉ መርህና ዓለም አቀፋዋዊ ስርዓት እንዲጠበቅ በማገዝ የበለጠ ይረዳል፡፡ አገሮች በዓለም አቀፉ ህግ መሠረት በመካከላቸው ያለውን እኩልነታቸውን እንዲጠብቁ ያግዛል፡፡ የመጠን፣ የሀብት፣ የታሪክ እና የፖለቲካ መዋቅር ልዩነት ሳይለይ ሁሉም አገሮች ያላቸውን እኩል ፍላጎት ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡”

ሞሊ ፊ ጦርነቱ የሚያስከትለውን የምጣኔ ሀብት ተጽእኖ ለማስተካከል መንግስታቸው እገዛ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ

“የነዳጅ ዋጋ፣ የሸቀጦች ዋጋ መጨመራቸውን እያየን ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ቀደም ሲል በነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጽእኖ ላይ ተደርበው የመጡ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ ይሁን እንጂ ከወዲሁ የተመጣጠነ የነዳጅና የሸቀጥ ዋጋ እንዲኖር የአቅርቦቱን ሰንሰለት ለማስተካከል እየሠራን ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ፕሬዚዳንት ባይደን የነዳጅ ዋጋን ለማስተካከል በነዳጅ ክምችት ዙሪያ ከሌሎች ዓለም አቀፍ መሪዎች ጋር ለመስራት ያወጡትን እቅድ ተመልክተናል፡፡ “

የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በአውሮፓ ያለው ግጭት ከአህጉሪቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደማይጎዳ ለአፍሪካ መንግስታት ማረጋጋጡን አስታውቋል፡፡

XS
SM
MD
LG