ዩክሬን ውስጥ የሚገኙ አፍሪካዊያን ደኅንነታቸው ሊጠበቅ ወደሚችሉ ሃገሮች እንዳያልፉ በዩክሬን ድንበር በኩል የመታገዳቸው ነገር በጥልቅ እየረበሻቸው መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር፣ የሴኔጎል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳልና የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህሜት አስታወቁ።
ሁለቱ ሊቃነመንበር ማምሻውን በጋራ ባወጡት መግለጫ በግጭት ጊዜ ሁሉም ሰው ዓለምአቀፍ ድንበሮችን የማቋረጥ መብት እንዳለው አስታውሰው አሁንም በዩክሬን ግጭት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ዜግነታቸውና ዘራቸው ግምት ውስጥ ሳይገባ የዚህ መብት ተገልጋይ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አፍሪካዊያን ተቀባይነት በሌለውና ከሌሎች ጋር ተመሳሳይ ባልሆነ ሁኔታ መያዛቸውን የሚገልፁ ሪፖርቶች አስደንጋጭ ዘረኛና ዓለምአቀፍ ህግን የሚጥስ አድራጎት መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጠቁመው ሁሉም ሃገሮች ዓለምአቀፍ ህጎችን እንዲያከብሩና ዘርን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ከጦርነት ለሚሸሹ ሁሉ ተመሳሳይ ርህራሄና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አጎራባች ሃገሮች ውስጥ ያሉ የአፍሪካ ኅብረት አባል መንግሥታት ኤምባሲዎች ከዩክሬን ጦርነቱን እየሸሹ ድንበር ለማቋረጥ የሚሞክሩ አፍሪካዊ ዜጎችንና ቤተሰቦቻቸውን ለመቀበልና አቅጣጫ ለማመላከት እያደረጉ ያሉትን ጥረት ሁለቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቃነመንበር አድንቀዋል።
ዩክሬን ውስጥ ተኩስ አሁኑኑ እንዲቆምና የሩሲያ ኃይሎች በሙሉ ከሃገሪቱ እንዲወጡ ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ዛሬ የሄዱ መልዕከተኞቿ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ሃገራቸውን በአስቸኳይ በአባልነት እንዲቀበላት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጠይቀዋል።
ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የዲፕሎማሲና ዘርፈብዙ ማዕቀቦችን ሩሲያ ላይ መጣሉን ቀጥሏል።
ከዩክሬን ጦርነቱን እየሸሸ የሚወጣው ሰው ቁጥር ከግማሽ ሚሊየን ማለፉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
ከዩክሬን የትምህርት ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ መሠረት በጥቅሉ 16 ሺህ ተማሪዎች ካሏቸው አሥር ዋና ዋና የሚባሉ የአፍሪካ ሃገሮች መካከል ሞሮኮ፣ ናይጀሪያና ግብፅ ትልቆቹ ናቸው።
ናይጀሪያዊያኑ ተማሪዎች አዶኒስ አዮ አዎላቢና ጄሲካ የሃርኪፍ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ ጄሲካ ከከተማዪቱ ከወጡት መሃል ሲሆን የገጠማቸውን ችግር ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ቀደምብለው እዛው ዩክሬን ውስጥ በእርስ ላይ ይገኙ የነበሩ ተማሪዎች ደግሞ በጭንቀት ውስጥ መሆናቸውና መውጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።