በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአዋጁን መቋረጥ ዩናይትድ ስቴትስና የመንግሥታቱ ድርጅት አደነቁ


ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ፓርላማ በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ፓርላማ በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታውን ማንሳቷን ዩናይትድ ስቴትስና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚያደንቁ ከቃል አቀባዮቻቸው በተናጠል የወጡ መግለጫዎች አስታውቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በፅሁፍ ባወጡት መግለጫ “እርምጃው እየተካሄደ ላለው ግጭት ሰላማዊ መፍትኄ ለማስገኘት በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰደ አንድ ሌላ ጠቃሚ እርምጃ ነው” ብለዋል።

ይኸው የኔድ ፕራይስ መግለጫ አክሎም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ያለ ክሥ የተያዙ ወይም የታሠሩ ሰዎች ሁሉ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቆ የሰዎቹ መለቀቅ ሁሉን አቀፍና ፍሬያማ ብሄራዊ ንግግር እንዲደረግ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች አመክልቷል።

መግለጫው በመቀጠል “የጥል ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ በተፈፀሙ ጥሰቶችና ረገጣዎች ላይ ሁሉ ግልፅ ምርመራዎች እንዲካሄዱ፣ ለግጭቱ በድርድር መፍትኄ ላይ እንዲደረስ ዩናይትድ ስቴትስ ከሁሉም ወገኖች ጋር መነጋገሯን ትቀጥላለች” ብሏል።

በሌላ በኩል የተባበሩት መግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱያሪች በዛሬው ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ስለኢትዮጵያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳትና የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ ስላላቸው አቋም ተጠይቀው ሲመልሱ ድርጅቱ ውሣኔውን “በጣም እንደሚያደንቀው” ተናግረዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ የተያዙና የታሠሩ ሰዎችን፣ የግጭቱን መቆም፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና ተጠያቂነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በዋና ፀሃፊው ስም የተናገሩት ዱያሪች የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ካወጡት መግለጫ ጋር የሚመሳሰል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ከጊዜው ቀድሞ እንዲቋረጥ የወሰነው ዛሬ ካካሄደው ክርክር በኋላ በሰጠው ድምፅ ነው።

XS
SM
MD
LG