በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን አነሳ


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በአስቸኳይ የተሰበሰበው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላለፉት ስድስት ወራት በሀገሪቱ ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንዲነሳ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 8/ 2014 ዓ.ም በአብላጫ ድምፅ ወስኗል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ ያስተላለፈው ጥር 18/2014 ዓ.ም ነበር።

ዛሬ በዚህ ውሳኔ ላይ ድምፅ ለመስጠት ከተገኙት 312 የምክር ቤት አባላት መካከል ስልሳ ሦስቱ መነሳቱን ሲቃወሙ ሃያ አንዱ ደግሞ ተአቅቦ አድርገዋል።

የውሳኔ ሐሳቡን የደገፉ የምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ማውጣት የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎት የነበረው ሁኔታ መቀየሩን ተናግረዋል።

የጸጥታ ስጋቶችን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል ።

የዐዋጁን መነሳት ያልደገፉት የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ህወሃት በአፋር ክልል ላይ ጥቃት በቀጠለበት እና በአማራ ክልል ላይም ተመሳሳይ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀ ባለበት ሁኔታ ውሳኔው መተላለፍ እንደሌለበት በመግለፅ ተቃውመዋል።

ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች እየፈጸመ ባለው ጥቃትን ንጹሐን ዜጎች እየተገደሉ ነው ሲሉም እነዚሁ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል ።

በሌላ በኩል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ስሙ ተደጋግሞ የተነሳውና ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሃት በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መነሳት ላይ ያለው ነገር የለም።

በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ ተደርጎ የነበረው ዐዋጅ ጥቅምት 21 /2014 ዓ.ም ፀድቆ የነበረ ሲሆን በሀገር ህልውና ላይ የተደቀኑትን አደጋዎች በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስርዓት ለመቋቋም አዳጋች በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አስፈላጊነት ተገልጾ ነበር።

አዋጁ በፀደቀበት ወቅትም የትግራይ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ እየተጠጉ እንደሆነ ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል። ቆይቶም በታኅሳስ ወር ለመደራደር ሁኔታዎችን ለማመቻቸ ጦራቸውን ወደ ኋላ መመለሳቸው የክልሉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ገልፀው ነበር።

በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ስር በርካታ የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እንደታሰሩ የመብት ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል። ካለፈው ታኅሣስ ወር ጀምሮ ደግሞ ብዙዎቹ መፈታት መጀመራቸውን ዛሬ አሶሼትድ ፕሬስ ዛሬ አስነብቧል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የኢትዮጵያ ፓርላማ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን አነሳ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:04 0:00

XS
SM
MD
LG