ዛሬ ደሴንና ኮምቦልቻን የጎበኙት የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ቆይታቸው የተደበላለቀ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናገሩ።
"አመራሮቹን አግኝቻለሁ እና የውዝግብ ምንጭ ተደርገው የሚቆጠረዉ ምንም ይሁን በቀላሉ ሊፈታ እንደሚችል ተስፋ ሰጥተውኛል" ብለዋል።
“በተመለከትኩት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ በደረሰዉ አላስፈላጊ ጉዳት መጠን አዝኛለሁ። ይህንን ጉዳት ማስቀረት ይቻል ነበር እና እየተመለስኩ ያለሁት በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው።” ብለዋል።
በሌላ ዜና የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋናጸሐፊ በደቡብ ወሎዋ ኮምቦልቻ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ርእሰ ም/ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ በኮምቦልቻ ከተማ በህወሓት ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ ትናንት በመቀሌ ከተማ ጉብኝት ማድረጋቸውን፣ በዓይደር ሪፌራል ሆስፒታል ተገኝተው በሆስፒታሉ የሚታየውን የመድኃኒት እጥረት መመልከታቸውና በተጨማሪም በተፈናቃዮች ማዕከልና ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ጎብኝተዋል።