በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሰብዓዊ መብት እና ኪነጥበብ


ሰብዓዊ መብት እና ኪነጥበብ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:19 0:00

በየዓመቱ ታህሳስ አንድ ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን "እኩልነት፣ ተበላላጭነትን ማስወገድ እና ሰብዓዊ መብትን ማስፋፋት" በሚል መሪህ ቃል ተከብሯል። ይህን ዓመታዊ በዓል አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ግንዛቤን ለማስፋፋት ያለመ የፊልም ፌስቲቫል በአዳማ፣ በሀዋሳና አዲስ አበባ ላይ ያካሄደ ሲሆን የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶችን የሚያነሱ የሀገር ውስጥ ፊልሞች ለእይታ በቅተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.አ.አ በ1948 ዓ.ም ያፀደቀው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ ሁሉም የሰው ልጆች በተፈጥሮአቸው እኩል የሆኑና የማይገሰሱ መብቶች እንዲሁም መሰረታዊ ነጻነቶች እንዳሏቸው አስቀምጧል። በዚህ መሰረት በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ የሰው ልጆች ያለ ዜግነት፣ የመኖሪያ ቦታ፣ ፆታ፣ የዘር፣ የሀይማኖት፣ የቋንቋ ወይም የሌላ መለያ ልዩነት፣ ሰው በመሆናቸው ብቻ እኩል የሆኑ መብቶች እንዳሏቸው የሚደነግግ ሲሆን፣ ድንጋጌው የፀደቀበት ታህሳስ አንድ ቀን፣ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን ተብሎ ይከበራል።

ይህ ቀን በኢትዮጵያም በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየ ቢሆንም መርሆውን 'እኩልነት' ላይ መሰረት ያደረው የዘንድሮ በዓል ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል በማዘጋጀት ለህብረተሰቡ የመወያያ መድረክ ፈጥሯል።

ለመሆኑ ሰብዓዊ መብትንና ኪነጥበብን ምን አገናኛቸው? የፌስቲቫሉ አዘጋጅ የሆነው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ራኬብ መሰለን አናግረናቸዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በግጭቶች እና በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያለፈች ባለችበት ወቅት በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የውይይት በር የሚከፍት የፊልም ፌስቲቫል መዘጋጀቱ ሀገሪቱ ካለችበት ቀውስ እንድትወጣ የሚያግዝ አንድ መንገድ መሆኑንም ያስረዳሉ።

በዚህ ሀሳብ መነሻ መሰረት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውና ከህዳር 28 እስከ ታህሳስ 1 2014 ዓ.ም የተካሄደው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል በአዳማ፣ በሀዋሳና በአዲስ አበባ ላይ የተካሄደ ሲሆን ሰባት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ርዕሶችን የሚያነሱ ፊልሞች ለዕይታ መቅረባቸውን ወይዘሮ ራኬብ ጨምረው ያስረዳሉ።

ለመጀመሪያ ግዜ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ አተኩሮ በተዘጋጀው ፌስቲቫል በቲያትርና በፊልም ሙያ ልምድ ያላቸው አዘጋጆች በማስተባበር እና በማማከር ተሳትፈዋል። ከነዚህ አንዷ የቲያትርና የፊልም ባለሙያ እንዲሁም የመዓዛ ፊልም ፕሮዳክሽን ስራ አስኪያጅ የሆነችው መዓዛ ወርቁ አንዷ ናት። በቅርብ ግዜ በብዙ ተመልካች ዘንድ ተወዳጅ የነበረው 'ደርሶ መልስ' ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ደራሲና ዳይሬክተር የሆነችው መዓዛ ውርቁ የኪነጥበብ መሰረቱ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ናቸው ትላለች።

መዓዛ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኪነጥበቡ ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ቅርበት ተገንዝቦ ከፊልም ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ፌስቲቫሉን ማዘጋጀቱ ትልቅ ጅማሮ መሆኑን ትገልፃለች። በፌስቲቫሉ ላይ ተመርጠው የቀረቡት ሙሉ፣ አጫጭር እና ዘጋቢ ፊልሞችም ይህንን አላማ ያንፀባረቁና ለውይይት የሚጋብዙ ናቸው ትላለች።

የፊልም ፌስቲቫል እንደ ድግስና ፌሽታ መቆጠር የለበትም የምትለው መዓዛ በተለይ ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች አጣብቂኝ ውስጥ ባለችበት ወቅት ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱ ወቅታዊ መሆኑን ትስማማለች።

ለሶስት ቀናት በተካሄደው በዚህ ሰብዓዊ መብቶች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያ የፊልም ፌስቲቫል ሰውነቷ፣ ቁራኛዬ፣ ብትሆንስ፣ ተጠርጣሪ፣ መንገደኛ ታሪኮች፣ አዲባናና ሰውነት የተሰኙ ፊልሞች የቀረቡ ሲሆን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑን ዓላማ በአግባቡ ያሳካ እንደነበር ራኬብ ይገልፃሉ።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በቀጣይ አመታት በሚደረጉ ፌስቲቫሎች ከፊልም በተጨማሪ ሌሎች የኪነጥበብ ስራዎችን የማካተት አላማ እንዳለው ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ ነግረውናል።

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የመጀምሪያው የፊልም ፌስቲቫል በሶስት ከተሞች ብቻ መደረጉን የሚገልፁት አዘጋጆች በቀጣይ በሚደረጉ ዝግጅቶች በመላው ኢትዮጵያ ላይ እንደሚደረጉ ገልፀውልናል።
ለአሜሪካ ድምፅ ዘገባ፣ ስመኝሽ የቆየ፣ ዋሽንግተን ዲሲ
XS
SM
MD
LG