በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተሰናባቹ 2013 ዓ.ም ፈታኝ ሁነቶች እና የአዲሱ አመት ተስፋ


Ethiopian New Year in Lalibela, central Ethiopia,
Ethiopian New Year in Lalibela, central Ethiopia,

ኢትዮጵያውያን እየተሰናበቱት ያለው 2013 ዓ.ም በብዙ ፈታኝ ሁነቶች የተሞላ ነበር። አመቱ ላለፉት አስር ወራት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ጨምሮ፣ በርካታ ግጭቶች፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የዋጋ ግሽበትና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የተስተናገዱበት ሆኖ አልፏል ። እነዚህን ተግዳሮቶች ምን ይመስሉ ነበር? በመጪው 2014 ዓመተ ምህረትስ ምን ይጠበቃል?

የተሰናባቹ 2013 ዓ.ም ፈታኝ ሁነቶች እና የአዲሱ አመት ተስፋ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:45 0:00

(ዝርዝሩን ከላይ ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ)

2013 ዓ.ም ለብዙ ኢትዮጵያውያን ከየትኛውም ግዜ የላቀ ፈታኝ አመት ሆኖ እያለፈ ነው። የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው ህወሃት እና በፌደራል መንግስቱ መሀከል በተፈጠረ የፖለቲካ ውጥረት የጀመረው አመት ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ የበርካቶች ህይወት የተቀጠፈበት፣ ንብረት የወደመበትና በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው እርዳታ የሚጠብቁበት አመት ሆኖ አብቅቷል። በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ የሚያገረሹ ግጭቶች፣ አለምን የሚያምሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝና በየጊዜው እያሻቀበ የሚሄደው የዋጋ ግሽበት ግለሰቦችን፣ ተቋማትንና ሀገርን እየፈተኑ ይገኛሉ።

ይህን መረሻ አድርገን 2013 እንዴት አለፈ ስንል ካናገርናቸው ምሁራን መሃከል የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነቶች መምህርና ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ኢትዮጵያ በውጣዊ ችግር ብቻ ሳይሆን በውጪ ግንኙነትም የተፈተነችበት አመት ነበር ይላሉ።

አመቱን ከዘለቀው ጦርነትና ግጭት ጎን ለጎን በ2013 ዓ.ም ለኢትዮጵያኖች ከባድ የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስና እያሻቀበ የሚሄደው የኑሮ ውድነት ነው። ሙያዊ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የገጠር ልማት አማካሪ እና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አምዲሳ ተሾመ- ወደ አዲሱ 2014 ዓ.ም. አብሮ እየተሻገረ ያለው ይህ የዋጋ ግሽበት ዋና ምክንያቱ ለግብርናና የፋብሪካ ምርቶች ትኩረት መነፈጉ መሆኑን ይገልፃሉ።

ዶክተር አምዲሳ እንዳሉት 2013 የግብርና ምርትንም አደጋ ላይ የጣለ አመት ነበር። በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በግጭቶች ምክንያት በመፈናቀላቸው፣ ከዚህ ቀደም አምራች የነበሩ ገበሬዎች ዘንድሮ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።በተደጋጋሚ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች የተከሰተው የአምበጣ መንጋና የጎርፍ አደጋም እንዲሁ በእርሻ ምርቶች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ዶክተር አምዲሳ "ይህ ብቻ አይደለም" ይላሉ።

የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር መንግስት እንደ የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ሩዝ፣ እና ስንዴ የመሳሰሉ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላልተወሰነ ግዜ ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡ አድርጓል። ለስድስት ወር ተፈቅዶ የነበረው ያለውጪ ምንዛሬ ወይምፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦችን የማስገባት ፈቃድም ለተጨማሪ ስድስት ወራት ተራዝሟል። እነዚህ ውሳኔዎች በግዜያዊነት ገበያውን ከማረጋጋት አንፃር ጠቀሜታ ቢኖራቸውም በመጪው አዲስ አመት ግን መንግስት ትልቅ የቤት ስራ እንደሚጠብቀው ዶክተር አምዲሳ ያሰምሩበታል።

በነዚህ ተደራራቢ ችግሮች እየተፈተነ ባለ ህብረተሰብ ላይ ኮቭድ 19 ወረርሽኝ እየተወ ያለው ጠባሳም ቀላል የማይባል ሆኖ ሳለ፣ ህብረተሰቡ ያጋጠመው በፓለቲካውም ሆነ በበሽታው ዙሪያ የሚሰራጩ የእውነተኛና ሀሰተኛ መረጃዎች መደበላለቅ፣ 2013 በርካቶችን ለአይምሮ ጭንቀት አጋልጧል ያሉን ደግሞ የአይምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት መዓዛ መንክር ናቸው።

ሀገርን ከዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማላቀቅና ዘላቂ ሰላምም ሆነ ልማት ለማምጣት የአይምሮ ጤና ከአካላዊ ጤና እኩል አስፈላጊ ነው። ታዲያ በርካታ ችግሮችን አዝሎ ወደ አዲሱ 2014 ዓ.ም. የሚሻገረው ማህበረሰብ የአይምሮ ጤናውን በምን መልኩ መጠበቅ ይችላል?

በኢትዮጵያ ዘርን፣ ሀይማኖትንና ማንነት ላይ ያተኮሩ ግጭቶችን ለማስቆም ሲንቀሳቀስ የቆየው የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በጳጉሜ ወር ለ5 ቀናት ሀገር አቀፍ ፀሎት እንዲካሄድ ማወጁን ተከትሎ የሁሉም ሀይማኖት አማኞች እንደየእምነታቸው ለአምስት ቀናት ፆምና ፀሎት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። የጉባኤው ሰብሳቢ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለም እነዚህ ቀናት ህብረተሰቡ ልቡን ለዕርቀ ሰላም እንዲከፍት ያደርገዋል ይላሉ።

ፈተና የበዛበትን 2013ን አልፎ ወደ አዲሱ 2014 ዓ.ም. ለመሻገር የጠፉትን ነገሮች በማስተዋል ማለፍ ያስፈልጋል የሚሉት ሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ በአመቱ ተስፋ ሰጪ የነበሩ እንደ ህዳሴ ግድብ ሙሌት አይነት ህዝብን አንድ የሚያደርጉ ክንዋኔዎችም እንደሚያስፈልጉ ያሰምሩበታል።

እነዚህን ፈተናዎች ያስተናገደውን 2013 ዓመተ ምህረትን ተሰናብተን አዲሱን አመት ተቀብለናል። ብዙዎችም 2014 ዓ.ም. የዕርቅና የአንድነት አመት እንዲሆን ተመኝተዋል - እኛም አዲሱ አመት የሰላምና የፍቅር ይሁን እንላለን።

XS
SM
MD
LG