በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተሰናባቹ 2013 ዓ.ም ፈታኝ ሁነቶች እና የአዲሱ አመት ተስፋ


የተሰናባቹ 2013 ዓ.ም ፈታኝ ሁነቶች እና የአዲሱ አመት ተስፋ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:45 0:00

ኢትዮጵያውያን እየተሰናበቱት ያለው 2013 ዓ.ም በብዙ ፈታኝ ሁነቶች የተሞላ ነበር። አመቱ ላለፉት አስር ወራት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ጨምሮ፣ በርካታ ግጭቶች፣ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የዋጋ ግሽበትና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የተስተናገዱበት ሆኖ አልፏል ። እነዚህን ተግዳሮቶች ምን ይመስሉ ነበር? በመጪው 2014 ዓመተ ምህረትስ ምን ይጠበቃል?

2013 ዓ.ም ለብዙ ኢትዮጵያውያን ከየትኛውም ግዜ የላቀ ፈታኝ አመት ሆኖ እያለፈ ነው። የትግራይ ክልልን ያስተዳድርበነበረው ህወሃት እና በፌደራል መንግስቱ መሀከል በተፈጠረ የፖለቲካ ውጥረት የጀመረው አመት ወደ ጦርነት ተሸጋግሮየበርካቶች ህይወት የተቀጠፈበት፣ ንብረት የወደመበትና በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው እርዳታ የሚጠብቁበትአመት ሆኖ አብቅቷል። በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ የሚያገረሹ ግጭቶች፣ አለምን የሚያምሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝናበየጊዜው እያሻቀበ የሚሄደው የዋጋ ግሽበት ግለሰቦችን፣ ተቋማትንና ሀገርን እየፈተኑ ይገኛሉ።

ይህን መረሻ አድርገን 2013 እንዴት አለፈ ስንል ካናገርናቸው ምሁራን መሃከል የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነቶችመምህርና ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ኢትዮጵያ በውጣዊ ችግር ብቻ ሳይሆን በውጪ ግንኙነትምየተፈተነችበት አመት ነበር ይላሉ።

አመቱን ከዘለቀው ጦርነትና ግጭት ጎን ለጎን በ2013 ዓ.ም ለኢትዮጵያኖች ከባድ የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስና እያሻቀበየሚሄደው የኑሮ ውድነት ነው። ሙያዊ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የገጠር ልማት አማካሪ እና የኢኮኖሚባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አምዲሳ ተሾመ- ወደ አዲሱ 2014 ዓ.ም. አብሮ እየተሻገረ ያለው ይህ የዋጋግሽበት ዋና ምክንያቱ ለግብርናና የፋብሪካ ምርቶች ትኩረት መነፈጉ መሆኑን ይገልፃሉ።

ዶክተር አምዲሳ እንዳሉት 2013 የግብርና ምርትንም አደጋ ላይ የጣለ አመት ነው። በሚሊየኖች የሚቆጠሩ አርሶአደሮችበግጭቶች ምክንያት በመፈናቀላቸው፣ ከዚህ ቀደም አምራች የነበሩ ገበሬዎች ዘንድሮ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።በተደጋጋሚ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች የተከሰተው የአምበጣ መንጋና የጎርፍ አደጋም እንዲሁ በእርሻ ምርቶችላይ ጉዳት አድርሰዋል። ዶክተር አምዲሳ "ይህ ብቻ አይደለም" ይላሉ።

የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር መንግስት እንደ የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ ሩዝ፣ እና ስንዴ የመሳሰሉ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችላልተወሰነ ግዜ ከቀረጥ ነፃ ሆነው እንዲገቡ አድርጓል። ለስድስት ወር ተፈቅዶ የነበረው ያለውጪ ምንዛሬ ወይምፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦችን የማስገባት ፈቃድም ለተጨማሪ ስድስት ወራት ተራዝሟል። እነዚህ ውሳኔዎች በግዜያዊነትገበያውን ከማረጋጋት አንፃር ጠቀሜታ ቢኖራቸውም በመጪው አዲስ አመት ግን መንግስት ትልቅ የቤት ስራእንደሚጠብቀው ዶክተር አምዲሳ ያሰምሩበታል።

በነዚህ ተደራራቢ ችግሮች እየተፈተነ ባለ ህብረተሰብ ላይ ኮቭድ 19 ወረርሽኝ እየተወ ያለው ጠባሳም ቀላል የማይባልሆኖ ሳለ፣ ህብረተሰቡ ያጋጠመው በፓለቲካውም ሆነ በበሽታው ዙሪያ የሚሰራጩ የእውነተኛና ሀሰተኛ መረጃዎችመደበላለቅ፣ 2013 በርካቶችን ለአይምሮ ጭንቀት አጋልጧል ያሉን ደግሞ የአይምሮ ጤና ባለሙያ የሆኑት መዓዛ መንክርናቸው።

ሀገርን ከዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማላቀቅና ዘላቂ ሰላምም ሆነ ልማት ለማምጣት የአይምሮ ጤና ከአካላዊ ጤና እኩልአስፈላጊ ነው። ታዲያ በርካታ ችግሮችን አዝሎ ወደ አዲሱ 2014 ዓ.ም. የሚሻገረው ማህበረሰብ የአይምሮ ጤናውን በምንመልኩ መጠበቅ ይችላል?

በኢትዮጵያ ዘርን፣ ሀይማኖትንና ማንነት ላይ ያተኮሩ ግጭቶችን ለማስቆም ሲንቀሳቀስ የቆየው የኢትዮጵያ የሀይማኖትተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በጳጉሜ ወር ለ5 ቀናት ሀገር አቀፍ ፀሎት እንዲካሄድ ማወጁን ተከትሎ የሁሉምሀይማኖት አማኞች እንደየእምነታቸው ለአምስት ቀናት ፆምና ፀሎት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። የጉባኤው ሰብሳቢ ሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለም እነዚህ ቀናት ህብረተሰቡ ልቡን ለዕርቀ ሰላም እንዲከፍት ያደርገዋል ይላሉ።

ፈተና የበዛበትን 2013ን አልፎ ወደ አዲሱ 2014 ዓ.ም. ለመሻገር የጠፉትን ነገሮች በማስተዋል ማለፍ ያስፈልጋል የሚሉትሊቀትጉሃን ቀሲስ ታጋይ በአመቱ ተስፋ ሰጪ የነበሩ እንደ ህዳሴ ግድብ ሙሌት አይነት ህዝብን አንድ የሚያደርጉክንዋኔዎችም እንደሚያስፈልጉ ያሰምሩበታል።

እነዚህን ፈተናዎች ያስተናገደውን 2013 ዓ.ምን ተሰናብተን አዲሱን አመት ተቀብለናል። ብዙዎችም 2014 ዓ.ም. የየዕርቅና የአንድነት አመት እንዲሆን ተመኝተዋል - እኛም አዲሱ አመት የሰላምና የፍቅር ይሁን እንላለን።

XS
SM
MD
LG