ከዘጠኝ ወራት በላይ ካስቆጠረውና የሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የእርስ በእርስ ግጭት በኋላ ሰብዓዊ ቀውስኑ በተመለከተ ግምገማ ያካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁኔታው አስጀፊ መሆኑን እና የሰዎቹን ሕይወት እና የአኗኗር ሁኔታቸውን ወደ አስከፊ ሁኔታ እንደቀየረው አስታወቀ።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሕዳር አራት ቀን የኢትዮጵያ ወታደሮች ትግራይን ከአማጺ ኃይሎች ላይ ከወሰዱ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአጣዳፊ ረሃብ ውስጥ መሆናቸውን የገለፀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት 400 ሺሕ ሰዎች ደግሞ በቸነፈር እየተሰቃዩ መሆናቸውን አስታውቋል። በተጨማሪም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክኒያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ሕይወት አደጋ ውስጥ በሆኑን ይፋ አድርጓል።
የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ቃል አቀባይ ዬንስ ላርከ ከ5.2 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሕይወት በዓለም አቀፍ ረድኤት ላይ ጥገኛ ነው መሆኑን ገልፀዋል። እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ የመጣውና የምግብ ዋስትና ሁኔታውን ለማስተካከል ጥቂት ግዜ ብቻ መቅረቱን የገለፁት ዬንስ ላርከ ፤ “ቁሳቁሶች የጫኑ ከባድ መኪኖች በየቀኑ መቀሌ ማረፍ አለባቸው። የትግራይ ሕዝብ የሚያስፈልገውን ለማሟላት ቢያንስ 500 ቁሳቁስ የጫኑ ከባድ መኪናዎች በየሳምንቱ ወደ ክልሉ መግባት እንደሚገባቸው የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ግምታቸውን ቢያስቀምጡ ይህ ግን መሆን አልቻለም” ብለዋል።
አያይዘም እስካሁን የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ 50 ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው ወደ ትግራይ የገቡት ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጀመሩትን የስድስት ቀናት ጉብኝት ያጋመሱት አዲስ ተሿዋሚው የመንግሥታቱ ድርጅት የአጣዳፊ ርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊዝ፤ ትግራይ ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ ሁኔታ ራሳቸው በአካል ተገኝተው ለመገምገም ወደክልሉ ይጓዛሉ።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ሲደርሱ የሚያዩት የተራቆተ ስቃይ ላይ ባሉ ሰዎች የተሞላ አካባቢ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ ቃል አቀባይ ዬንስ ላርከ እንደሚናገሩት ሲቪሎች በተዋጊዎቹ ኃይሎች ለተደራራቢ የጭካኔ አድራጎት እና እንግልት ተዳርገዋል።
"ግጭቱ ከተጀመረ አንስቶ ሲቪሎች ላይ የሚዘገንኑ ጥቃቶች እንደተፈጸመ ሪፖርቶች አመልክተዋል፤ በስፋት እና በተቀነባበረ መንገድ ወሲባዊ ጥቃት በጦርነት መሳሪያነት ውሏል፤ ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ ከአንድ ሽህ ስድስት መቶ በላይ ወሲባዊ እና ሌሎችም ጾታ ተኮር ጥቃቶች ሪፖርት ተደርገዋል። የጤና ጥበቃ ተቋማት የጥቃት እና ዝርፊያ ዒላማ ሆነዋል።" ብለዋል።
ትግራይ ውስጥ ካሉ 40 ሆስፒታሎች ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ያሉት 16 ብቻ ናቸው። ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸሙባቸው ሴቶችና ልጃገረዶች የህክምና ርዳታ ፍለጋ ቢወጡ ያለው እጅግ ውሱን ስፍራ ነው ወይም ደግሞ ጭራሹንም የለም "ሲሉም አክለው አስረድተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት እና የግል ተቋማት ሥራቸውን የሚሠሩት እጅግ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ የተናገሩት ቃል አቀባዩ ትግራይ ውስጥ ቢያንስ 12 የረድዔት ሠራተኞች እንደተገደሉ እና ከመካከላቸው ሦስቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሰኔ 24 ቀን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የተገደሉት የግብረ ሰናዩ ድርጅት የድንበር የለሽ ሃኪሞች ሰራተኞች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
ሌላው ደግሞ የገንዘብ ችግር መሆኑን ቃል አቀባዩ አንስተዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት መሥሪያ ቤቶች እስከዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ማብቂያ ባለው ጊዜ ነፍስ አድን ሥራዎችን ለማከናወን ከ430 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ነው አስታውቀዋል።