በዛሬው ዕለት ከጎንደር ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት የተበረከተለት የሙዚቃው ሰው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ “ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ እየተሻገረ ባለ ሙዚቃዊ ተፅኖ ለትውልድ ተምሳሌት መሆን የቻለ ” እና “ስለ ሃገር ብሔራዊ ክብር በሥራዎቹ የተሟገተ” በሚል ተወድሷል።
በክብር ዶክትሬት አሰጥታ ሥነ ስርዓቱ ላይ ስለ አርቲስት ቴዲ አፍሮ የተናገሩት የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደ ወይን፤ “ታላላቅ ብሔራዊ አጠይቆ ያላቸውን ነገረ ጭብጦች በሙዚቃዊ ሥራዎቹ ውስጥ በማንሳት ታሪክና ፍልስፍናን ሙግት የፈጠረ ነው” ብለውታል።
አያይዘውም “ስለ ሃገር ብሔራዊ ክብር በሥራዎቹ የተሟገተ፣ ለሙዚቃ ሁለንተናዊ ክብር፣ለፈጠራና ለሥነ ምግባርም አረያ መሆን የቻለ የጥበብ ሰው ነው” ሲሉ አሞግሰውታል።
የክብር ዶክትሬቱን ከተቀበለ በኋላ ንግግር ያደረገው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፤ “አገራችን ከገጠማት እና ሊገጥማት ከሚችለው ማንኛውም ከባድ አደጋ በድል ወጥታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።” ብሏል።
የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው በዚሁ ስነሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፤ “ኢትዮጵያን እኛ አባይ ግድባችንን ወሳኝ በሆነ ወቅት ቁልፍ መልዕክት ባለው ሙዚቃ ለፈጠርከው የአንድነት ስሜት እና ወኔ ላመሰግንህ እወዳለሁ።” ብለዋል።
(ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)