በህወሓት የሚመራውና ራሱን "የትግራይ ኃይል" ብሎ የሚጠራው አካል የዋግ ኽምራ ልዩ ዞን አበርገሌን አካባቢ መቆጣጠሩን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የኒሯቅ ከተማና ዙሪያው ኗሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ዞኑ ከተማ ሰቆጣ መሰደዳቸውን ገለጹ።ተፈናቃዮቹ በምግብና በመጠለያ እጥረት ለችግር መጋለጣቸውን ጠቅሰው መንግሥትና ሕዝብ እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል፡፡
ሰራዊቱ ከአካባቢው መውጣቱን ተከትሎ በበርካታ በሺሽዎች የሚቆጠሩ የአበርገሌ አካባቢ ኗሪዎች ወደ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና ከተማ ሰቆጣና አጎራባች ወደሆኑት ዝቋላና ሰቆጣ ወረዳዎች መሰደዳቸው ነው የተሰማው፡፡
የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በስልክ ያናገራቸው አስተያየት ሰጭዎች ከአበርገሌ ከተማ ኒሯቅ እስከ ሰቆጣ 67ኪ.ሜ በእግራቸው ለመጓዝ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ ከኒሯቅ ሰቆጣ ለመድረስ የሦስት ቀናት አስቸጋሪ ጉዞ ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ "አካባቢውን ለቀን ስንወጣ ያፈራነው ሃብትና ንብረት ተዘርፏል፣ እህሉም እንዲወድም ተደርጓል" ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ፡፡
ሰቆጣ ከተማ ከገቡም በኋላ በቀዝቃዛው የዓየር ንብረት፣ በምግብና በማረፊያ እጥረት መጎዳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ተፈናቃዮቹ፤ “መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ሰብዓዊ ድጋፍ ያድርግልን፣ አካባቢያችንም ተረጋግቶ ወደ ቀያችን እንመለስ” የሚል ጥያቄ አላቸው፡፡
የብሔረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ መልካሙ ደስታ ፤ባልተጠበቀ አጋጣሚ ሰራዊቱ ለቆ መውጣቱና በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተፈናቀለው መምጣታቸው ድጋፍ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ውስብስብ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
(ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)