በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሕግ ውጭ የታሠሩ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሕግ ውጭ የታሠሩ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:49 0:00


በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ። ኮሚሽኑ ሐምሌ 8/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ በሲቪል ሰዎች ላይ ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ እንግልትና እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት፣ የሕይወት መጥፋት እና መሰል ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳስቡት ገልጿል፡፡

ሕጻናትን ለውትድርና መጠቀምን የሚያመላክቱ መረጃዎች መኖራቸውንም አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም፤ ሕወሓት ህጻናትን መልምሎ ለውትድርና በመጠቀም ላይ እንደሚገኝ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ሐምሌ 4 በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ ሦስት የትግራይ ተወላጆች በድንገት በተሰባሰቡ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ ስለመገደላቸውም ጥቆማዎች እንደደረሱት አስታውቋል፡፡ኮሚሽኑ በመግለጫው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር መፈጸሙን በተመለከተ የደረሱትን መረጃዎች እየተከታተለ እንደሚገኝም ይፋ አድርጉኣል። እነዚህን ጉዳዮች በማጣራት ላይ እንደሚገኝ የገለፁት የኮሚሽኑ ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ እና ቃል አቀባይ አሮን ማሾ ምርመራው ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በተያያዘ መረጃ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ባወጣው መግለጫ፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በፖሊስ መያዛቸውን ገልጾ ድርጊቱ እንዲቆም እና ሁሉም እስረኞች ወንጀል ከፈጸሙ በፍጥነት ክስ እንዲመሰረትባቸው አሊያም ወዲያውኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁም አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው በዚሁ መግለጫ በታሳሪዎችና በምርኮኞች ላይ የሚፈጸሙ ኢሰብአዊ አያያዞች፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ሕጻናትን ለውትድርና መጠቀምን የሚያመላክቱ መረጃዎች መኖራቸውንም አንስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የተለያዩ ባለስልጣናትም፤ ሕወሓት ህጻናትን መልምሎ ለውትድርና በመጠቀም ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሐምሌ 8/2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ላይ ሕወሓት ሕጻናትን ለጦርነት መልምሎ የማሰለፍ ተግባር በግልጽ ማከናወኑን ጠቅሰው፣ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ድርጊቱን በዝምታ ከመመልከት ባለፈ አንዳንድ ሚዲያዎች በአዎንታዊነት መዘገባቸውንም ተናግረዋል፡፡

“በጦር ወንጀል ዓለም የፈረጃቸውን ሕፃናትን ለጦርነት የመመልመልና የማሰልፍ እንቅስቃሴ በግላጭ በሌላኛው ወገን እየተደረገ በኢግዚብትነት እየታየ ዓለም አቀፍ ሚዲያውም ሆነ ሌሎች መንግሥትን በተለያየ መንገድ ሲወቅሱና ሲከሱ የነበሩ አካላት ሁሉም ሰው ሊያወግዘውና ስህተት ነው ብሎ ሊቀበለው የሚገባ ጉዳይ ተፈፅሞ እያለ ባላየና ባልሰማ የማለፍ ዝንባሌዎች ታይተዋል። አንዳንድ የምዕራብ ሚዲያዎች ይህንኑ አይተው እንደ ወታደራዊ ሚዛን ማስተካከያ እየተጠቀሙበት መሆኑን በማጉላት በአዎንታ መልክ ለመዘገብ ያሳዩት ዝንባሌም ጎላ ያለ ትዝብት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።” ብለዋል።

ሕወሓት ሕጻናትን ለጦርነት ያሰልፋል ከመባሉ ጋር በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ስላሉት መረጃዎች የተጠየቁት የኮሚሽኑ ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ እና ቃል አቀባይ አሮን ማሾ፣ መረጃዎች መኖራቸውን እና ማጣረት እየተደረገባቸው መሆኑን ገልፀው፤ “አሁን ያንን ይፋ ማድረግ አልችልም ግን እያጣራን ነው። መረጃዎች አሉ ግን ማጣራት የሚያስፈልገው ጉዳይ ስለሆነ አጣርተን እንደጨረስን ብንናገር ይሻላል” ብለዋል።

በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይ እና የሕወሓት ተቃዋሚ ናቸው በሚል በሲቪል ሰዎች ላይ እንደተወሰዱ የሚነገሩ የግድያና የአፈና እርምጃዎችም እንደሚያሳስቡት በመግለጫው ያነሳው ኮሚሽኑ፣ በአላማጣና አካባቢው በድጋሚ ያገረሸውን ግጭት ተከትሎ እየተፈጸሙ ነው ከተባሉ የበቀል ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰዎች መፈናቀል መኖሩንም ጠቁሟል፡፡

ቴሌኮምዩኒኬሽንና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸው የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሥራውን አዳጋች ያደረገው ቢሆንም፣ ክትትሉን እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡ ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ፣ ወረታ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ሦስት የትግራይ ተወላጆች በድንገት በተሰባሰቡ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ ስለመገደላቸው ለኮሚሽኑ የደረሱት ጥቆማዎች እንደሚያመለክቱም መግለጫው አብራርቷል።

የኮሚሽኑ ከፍተኛ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ እና ቃል አቀባይ አሮን ማሾ፣ “እሱንም እንደተከሰተ ማረጋገጥ ችለናል። ነገር ግን እሱም ቢሆን ተጨማሪ ምርመራ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። የሕወሃት መከላከያ ኃይሎች በወሰዱት የጥቃት እርምጃ የፎገራ ነዋሪዎች አባላት የሆኑ የእርሻ ቡድን አባላት እንደዚሁም የወረዳው የሰላም ፀጥታ ኃላፊ መገደላቸው ከተነገረ በኋላ ነው የተከሰተው የማጣራቱ ሥራ እንደቀጠለ ነው። ካጠናቀቅን በኋላ ይፋ እናደርጋለን ” ብለዋል።

የፎገራ ወረዳና የአካባቢው የፀጥታና የአስተዳደር ኃላፊዎች በወሰዱት አፋጣኝ እርምጃ ሁኔታው የተረጋጋና ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል፡፡

ሌላው ኮሚሽኑ በመግለጫው ያነሳው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት እና እንግልት እንደሚፈጸም የሚደርሱትን መረጃዎች እየተከታተለ እንደሚገኝ የሚገልጽ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ አመራሮች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪ በቅርቡ ባደረጉት ውይይት፣ በአዲስ አበባ ሆነው በሽብር የተፈረጀውን ሕወሓትን የሚደግፉ ግለሰቦች መኖራቸውን ገልጸው፣ እነዚህ ግለሰቦች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ገልጸው ነበር፡፡

“እስካሁን ድረስ ያለውን ትዕግስትና ሕዝቡን ከጥቃት ፈፃሚው ቡድን ለመለየት የተደረገውን ጥረት አብዛኛው ሰው ይረዳል ብለን እናስባለን። ያልተረዱና ጊዜና አመቺ ሁኔታ የሚጠብቁትን ግን ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ከፌዴራል ፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሕግ አግባብ ውጭ ስለመታሰራቸው ያነሳቸው ሰዎች ከሕወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸው ስለመሆናቸው እና ስለቁጥራቸው ገና የማጣራት ሥራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አሮን “ቁጥሩን መግለፅ አልችልም ምክኒያቱም እሱንም እያጣራን ነው።” ብለዋል።

የሚድያ ሰራተኞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች ከአዲስ አበባ ውጭ ወደሚገኙ ስፍራዎች እየተወሰዱ ስመሆናቸውም ጥቆማዎች እንደደረሱት ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ በስፋት የሚደመጡ ያላቸው የጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች ሁኔታውን ሊያባብሱና ብሎም በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ትስስር ሊያላሉ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጾ፣ በየትኛውም አካባቢ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁና በነዚህ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ያደረሱና ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች የፈጸሙ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡም ጠይቋል፡፡

በተያያዘ መረጃ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ባወጣው መግለጫ፣ ሕወሓት መቀሌን በድጋሚ መቆጣጠሩን ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በፖሊስ መያዛቸውን አስታውቋል፡፡ አምነስቲ ታስረው ከተፈቱ ግለሰቦች፣ ከሕግ ባለሞያዎች እና ከሌሎች ምስክሮች ስለጉዳዩ ማስረጃ ማግኘቱን ገልጿል፡፡

በፖሊስ የሚፈጸመው የእስር ተግባር እንዲቆም እና ሁሉም እስረኞች ወንጀል ከፈጸሙ በፍጥነት እንዲከሰሱ እና ፍትሃዊ የፍርድ ሂደት እንዲሰጣቸው አሊያም ወዲያውኑ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁም አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳስቧል፡፡

ከትግራይ ተወላጆች በተጨማሪ የታሰሩ አክቲቪስቶች እና ጋዜጠኞችም መኖራቸውን ገልጾ መንግሥትም የታሰሩ ሰዎች የሚገኙበትን ቦታ ለቤተሰቦች ማሳወቅ እና ከጠበቆችና ዘመዶቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻችም ጠይቋል፡፡

XS
SM
MD
LG