የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ሕወሓትን የትግራይ ክልል መንግስት እንዲሁም በድርጅቱ የሚመራውን ኃይል የትግራይ መከላከያ ኃይል በሚል ስያሜ እንዳይጠቀሙ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፣ “ሕወሓትን የክልል መንግስት ማለት እና በክልል ደረጃ የመከላከያ ኃይል የሚል ስያሜ መጠቀም የተወካዮች ምክር ቤት ስልጣንን አለማከበር ነው ሲሉ ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን ስያሜዎች በሚጠቀሙ ሚዲያዎች ላይ ባለስልጣኑ ፈቃድ እስከመሰረዝ እርምጃ እንደሚወስድ አቶ መሀመድ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ጋር የሚጻረሩ ስያሜዎችን እንዳይጠቀሙ አሳስቧል፡፡
ባለስልጣኑ በትግራይ ክልል ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በመደበኛም ሆነ በበይነመረብ የሚሰሩ ዜናዎች እና ፕሮግራሞች ላይ ባደረገው ክትትል ሕግን ያላከበሩ አዘጋገቦችን መመልከቱን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀውን ህወሓትን የትግራይ ክልል መንግስት እንዲሁም በሕወሓት የሚመራውን ኃይል የትግራይ መከላከያ ኃይል በሚል ስያሜ መጠቀም ዋነኛው ሕገወጥ ተግባር መሆኑንም ነው ያስታወቀው፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፣ ሕወሓትን የክልል መንግስት ማለት እና በክልል ደረጃ የመከላከያ ኃይል የሚል ስያሜ መጠቀም የተወካዮች ምክር ቤት ስልጣንን አለማከበር ነው ሲሉ ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡“በኢትዮጵያ ሕግ ከፍተኛው የሕግ ወይም የሥልጣን ኃይል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በትግራይ ያለውን የሕወሃት ኃይል በሽብር የፈረጀው ኃይል ነው እኛ አሁን በየትኛውም እንደሚደረገው ሕጉን እና ሕጉን መሰረት አድርገን ምላሽ መስጠት ስላለብን ነው። ሁለተኛ በኢትዮጵያ ውስጥ ትግራይ የኢትዮጵያ ወይም የፌደራል ዴሞክራቲክ አንድ አካል ነች። ስለዚህ የትኛውም ክልል የራሱ መከላከያ ኃይል አለው የሚል የሕግ ማዕቀፍ የለም። መከላከያ የሚለው ሐሳብ እራሱ ከአንዲት ሉዓላዊት ሃገር ጋር አብሮ የሚነሳ ሐሳብ ነው። ሕግ ማስከበር ከተከናወነ በኋላ የመጣው ሕገወጥ የሆነው ኃይል ለእራሱ ለሚንቀሳቀሰው የሰጠው ስያሜ እንደ ሕጋዊ ስያሜ አድርጎ መሄድ የሕዝብ ተወካዮችን ሥልጣን አለመቀበል ነው።” ብለዋል።
ሕወሓትን የክልል መንግስት ማለት እና በድርጅቱ የሚመራውን ኃይል የትግራይ የመከላከያ ኃይል በሚል ስያሜ መጠቀም የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፣ የሀገር ደህንነትን እና የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የሚጎዳ ነው ሲል ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡ እነዚህን ስያሜዎች በሚጠቀሙ ሚዲያዎች ላይ ባለስልጣኑ ፈቃድ እስከመሰረዝ እርምጃ እንደሚወስድ አቶ መሀመድ ተናግረዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ም/ ቤት ጥቅምት 2013 ዓ/ም የቀድሞው የትግራይ ክልል መንግስት የሕወሓትን ሕጋዊነት ሽሮ አዲስ ጊዚያዊ አስተዳደር ቢያቋቁምም፣ መቀሌን በድጋሚ የተቆጣጠረው ሕወሓት ግን ራሱን የትግራይ ክልል ሕጋዊ መንግሥት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ በሕወሓት የሚመራው ኃይል ደግሞ ራሱን የትግራይ መከላከያ ኃይል በሚል ስያሜ መግለጽ ከጀመረ ቆየት ብሏል፡፡
ስያሜዎቹ ለሚዲያ ፍጆታ እንዳይውሉ ያስጠነቀቀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን፣ በክልሉ ምርጫ እስኪካሄደ ድረስ ትግራይን እንዲመራ ስልጣን የተሰጠው ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሆነም ገልጿል፡፡