(ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ በእርዳታ አቅርቦት ሰበብ ሕወሓትን የሚያስታጥቁ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪዎች መኖራቸውን በመጠቆም፣ መንግሥት አንዳንድ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶችን ከሃገር ሊያስወጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ሕወሓት ጦርነት ለመቀስቀስ ትንኮሳ እየፈጸመ እንደሚገኝም የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን፣ ትንኮሳው ከቀጠለ መንግሥት የተኩስ አቁም ውሳኔውን በማጤን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ተናግውረዋል፡፡ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብም የሕወሓትን ድርጊት እንዲያወግዝ ጠይቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ የትግራይ ክልልን ወደ መምራት ዳግም መመለሳቸውን የገለጹት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል፣ የክልሉ ሕዝብ መብቶቹን ሙሉ በሙሉ ለማስከበር የጀመረውን ትግል እንደሚቀጥል ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በዛሬው መግለጫቸው ኢትዮጵያ በታሪኳ ከተጋፈጠቻቸው አስከፊ ፈተናዎች አንዱን በአሁኑ ወቅት በመጋፈጥ ላይ መሆኗን እና ሀገሪቱ እንድትበተን ጫናዎች እየበረቱ እንደሚገኙም አስታውቀው ወዳጅ ሀገራት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በትግራይ ካለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የጸደቀውን የውሳኔ ሀሳብ “በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የተደረገ ቅድመ ሁኔታ” በማለት አምባሳደር ሬድዋን በጽኑ አውግዘዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አወጅኩ ያለውን የተናጥል ተኩስ አቁም ተከትሎ ከተፈጠሩ ክስተቶች ጋር በተያያዘ የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ምላሾች እና የመንግስትን ቀጣይ ውሳኔ በማስመልከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡