በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ከተጠናቀቀ፣ ግብጽና ሱዳን ፊታቸውን ወደ ትብብር ይመልሳሉ” - አምባሳደር ዲና ሙፍቲህ


 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የተመድ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመለስ በጸጥታው ምክር ቤት አባላት መወሰኑ ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ከተጠናቀቀ፣ ግብጽና ሱዳን ፊታቸውን ወደ ትብብር ይመልሳሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደር ዲና ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ ደግሞ፣ ለሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት የአየር ክልል ሙሉ በሙሉ መፈቀዱን አስታውሰው፣ ነገር ግን ሁሉም አውሮፕላኖች ሲገቡም ይሁን ሲወጡ አዲስ አበባ ላይ እንደሚፈተሸ ተናግረዋል፡፡ ከተኩስ አቁም ስምምነት ጋር በተያያዘ፣ሕወሓት ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች “ሊሆኑ የማይችሉ” በማለት ተቀባይነት እንደሌላቸውም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በጸጥታው ምክር ቤት የተካሔደው ስብሰባ ዋነኛው ነው፡፡ ሁሉም የጸጥታው ምክር ቤት አባላት የግድቡ ጉዳይ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመለስ መግለጻቸውንያነሱት አምባሳደር ዲና፣ ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“ይህ አጀንዳ ትላንትና አሜሪካን ሃገር በፀጥታው ምክር ቤት እንዳልሆነ ሆኗል። አጀንዳው ከዚህ በኋላ በፀጥታው ምክር ቤት ሊታይ አይችልም ማለት ይቻላል። ዐሥራ አምስቱም ማለት ይቻላል የድምፅ ቃናቸው ይለያይ እንጂ ወደዛው እንዲወሰድ ወስነዋል። እኛ ይህንን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስኬትነው ብለን ነው የወሰነው። ምክኒያቱም የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ የሆኑቱንም ያልሆኑትም አባላት በተለያየ መልኩ በተናጥልም ሆነ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ስናነጋግራቸው ነበር የቆየነው እንግዲህ የዚህን ውጤቱን አይታችሁታል።” ብለዋል።

በሂደት ላይ የሚገኘው ሁለተኛው የግድቡ ሙሌት ከተጠናቀቀ፣ ግብጽና ሱዳን ፊታቸውን ወደ ትብብር ይመልሳሉ ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ከዚህ በኋላ የግድቡን ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት አይወስዱትም ብለዋል።፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከሚገኙ የናይል ተፋሰስ ሃገራት አምባሳደሮች ጋር ባደረገው ውይይት የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ወደ ተመድ የጸጥታው ምክር ቤት መሄዱ ትክክል እንዳልሆነ ከመግባባት ላይ መደረሱን እና የአረብ ሊግ ጉዳዩ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዲሄድ ማድረጉለአፍሪካ ሕብረት እና ለአፍሪካ ሃገራት ያለውን ንቀት እንደሚያመለክት አምባሳደሮቹ ማንሳታቸውንም ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር ዲና ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ ደግሞ፣ ለሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት የአየር ክልል ሙሉ በሙሉ መፈቀዱን አስታውሰው፣ ነገር ግን ሁሉም አውሮፕላኖች ሲገቡም ይሁን ሲወጡ አዲስ አበባ ላይ አርፈው ፍተሸ እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል፡፡ ፍተሻውከአውሮፕላኖች በተጨማሪ መኪኖችን እና ግለሰቦችንም እንደሚጨምርም አክለው ገልጸዋል፡፡

ለሰብዓዊ እርዳታ አድራሾች ሙሉ ለሙሉ የበረራ ፍቃድ መሰጠቱን የተናገሩት አምባሳደር ዲና ሙፍቲህ ነገር ግን ለበረራው ፈቃድ የተሰጠው በአዲስ አበባ በኩል መሆኑን ጠቁመዋል። “እዚህ ደርሰው ከዚህ ነው ወደዚያ የሚሄዱት። ከዚያ ሲጨርሱም በዚህ ነው የሚያልፉት።” ያሉ ሲሆን ፤“ከአዲስ አበባ ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ ፍተሻ ይደረጋል። ይህ ደግሞ በየትኛውም ዓለም አቀፍ መመዘኛ የሚደረግ ነው።” ብለዋል።

ለሃገር ደህንነት ሲባል የትኛውንም ዓይነት መጓጓዣዎች መፈተሽ መብት መሆኑንም አክለዋል።

የፈረሰውን የተከዜ ድልድይ መልሶ የመገንባት ሥራም መጀመሩን አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ከተኩስ አቁም ስምምነት ጋር በተያያዘ፣ የትግራይ መንግሥት ነኝ ያለው አካል ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች “ሊሆኑ የማይችሉ” በማለት ተቀባይነት እንደሌላቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት የኤምባሲዎቹን ቁጥር እንደሚቀንስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ማንሳታቸውን ተከትሎ፣ ኤምባሲዎች እየተዘጉ ስለመሆናቸው በማሕበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች ሐሰት መሆናቸውንም አምባሳደር ዲናገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማሻሻያ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን በመጠቆም በሂደት ሊታጠፉ የሚችሉ ኤምባሲዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግን ጠቁመዋል፡፡

በተቀናጀ መንገድ ከሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን የመመለሱ ሥራ የቀጠለ ሲሆን፣ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እስከትናንት ሐምሌ አንድ ድረስ 21 ሺህ 182 ዜጎች መመለሳቸውም ተገልጿል፡፡ አምባሳደር ዲና ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውም ዜጎች ከሳዑዲእንዲመለሱ በመደረግ ላይ መሆኑን አንስተው፣ “ይህም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማብዛት የሚደረግ ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡


XS
SM
MD
LG