የጸጥታው ምክር ቤት በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ዛሬ የሚያደርገው ስብሰባ የተለየ ለውጥ እንደማያመጣ ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ባለሞያዎች ገለጹ።
“የሕዳሴው ግድብ ከዓለም አቀፍ ጸጥታ ጋር የሚገናኝ አይደለም” የሚሉት የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ እና የባለሞያዎች ቡድንሰብሳቢ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ጉዳዩ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሔዱን ተቃውመዋል፡፡
ግብጽ እና ሱዳን የሕዳሴ ግድቡን ጉዳይ ለውስጥ ችግራቸው ማስተንፈሻነት እንደሚጠቀሙ የሚገልጹት የዲፕሎማሲ እና ዓለማቀፍግንኙነት መምሕሩ እንዳለ ንጉሴም፣ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን የማየት ሕጋዊ መሰረት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ፣ “የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ከምክር ቤቱኃላፊነት ውጭ ነው” በማለት ኢትዮጵያ ጉዳዩ ወደ ምክር ቤቱ ማምራቱን እንደማትደግፍ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግድቡን የመሙላት ድርጊት ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ እንደሆነ ግብጽ እና ሱዳን ይከሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሙሊቱን የምታከናውነው ሀገራቱ በፈረሙት የመርሆች ስምምነት መሰረት መሆኑን የሚገልጹት ኢንጂነር ጌዲዮን፣ የሁለቱ ሀገራት ክስ ዓለምአቀፉን ማሕበረሰብ የማደናገር ሙከራ እንደሆነ ነው ተናግረዋል፡፡ የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻእንደሚጠናቀቅም ገልፀዋል፡፡
(ሙሉ ዘገባውን ከያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)