በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ ከሚገኙ አራት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፖች የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአምስት መቶ በላይ ወጣት ወንዶች እና ሴቶችን አስረው ወስደዋል ሲሉ ሦስት የረድዔት ሰራተኞች እና አንድ ሃኪም መናገራቸው ሮይተር ዘገበ።
ወታደሮቹ ሰኞ ማታ አምስት ሰዓት ላይ ካምፖቹን በኃይል ወርረው በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎችን አፍሰው መኪና ላይ ጭነው ወስደዋቸዋል፣ አብዛኞቹ ወንዶች ተደብድበዋል ስልክና ገንዘብ ተወርሶባቸዋል ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
ከተያዙት ውስጥ አንድ የሰባ ዓመት አዛውንት እና አንድ ማየት የተሳናቸው ሰው ያሉበት መሆኑን የተናገረ የካምፑ ነዋሪ በጊዜው ትደብቆ እንደነበር እና እሱ ካለበት ካምፕ አራት መቶ ነዋሪዎች መወሰዳቸውን እንደተናገረ ሮይተርስ አመልክቷል።
ከኢትዮጵያ ወታደራዊ ቃል አቀባይ እና በክልሉ ካለው የመንግሥታዊ ግብረ ኃይል ኃላፊ ምላሽ ለማግኘት እንዳልቻለ የጠቀሰው ዘገባው ሆኖም ከተማዋ የምትገኝበት ዞን ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ቴዎድሮስ አረጋይ ስለጉዳዩ ብዙ መረጃ ባይኖረኝም በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች መወሰዳቸውን አረጋግጣለሁ እንዳሉ ገልጿል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በበኩላቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ታፍሰው የሚታሰሩበት ምክንያት አይታየኝም። ይሄ የህወሓት ፕሮፓጋንዳ ነው ማለታቸውን ዘገባው አክሎ፣ ታፍሰው ትወስደዋል ያላቸው ተፈናቃዮች ቤተሰቦች ትናንት ጠዋት በተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ቢሮዎች ደጃፍ ተቃውሟቸውን እንዳሰሙ አክሎ አውስቷል።