በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኪንሻሳ የኅዳሴ ግድብ ድርድር ያለስኬት ተበተነ


የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር በሆኑት የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ-አንቷን ሺሴኬዲ አደራዳሪነት ዋና ከተማዪቱ ኪንሻሳ የተደረገ ውይይት
የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር በሆኑት የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ-አንቷን ሺሴኬዲ አደራዳሪነት ዋና ከተማዪቱ ኪንሻሳ የተደረገ ውይይት

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር በሆኑት የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ-አንቷን ሺሴኬዲ አደራዳሪነት ዋና ከተማዪቱ ኪንሻሳ ላይ ትናንት ተጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ ድርድር ያለስኬት ተበተነ።

ስለጉዳዩ ዛሬ የተጠየቁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱያሪች “ልዩነቶችን የማቻቻልንና የመተባበርን አስፈላጊነት በበቂ ሁኔታ ላጎላው አልችልም” ብለዋል።

የተጨበጠ ስምምነት ላይ ለመድረስ ወገኖቹ አበርትተው መጣራቸውን እንዲቀጥሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ጥሪ እንደሚያደግ ዱያሪች አመልክተው በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነታቸው ወገኖቹን እንደገና ለማገናኘት ፕሬዚዳንት ሺሴኬዲ ስላደረጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

የወገኖቹን ጥረቶች ለመደገፍም የመንግሥታቱ ድርጅት አሁንም ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ እንደሚያረጋግጥ አስታውቀው “እኔ ይህንን ልተው፤ አንተም ይህንን ተው” የማለት አካሄድና የትብብርን አስፈላጊነት በድጋሚ አንስተው አሳስበዋል።

ለድርድሩ መስተጓጎል “ከኢትዮጵያ በኩል በቅንነት ለመነጋገር የፖለቲካ ፍላጎት የለም” ሲል የግብፅ ወገን መክሰሱን ስለሁኔታው ዋና ፀሃፊው ምን እንደሚያስቡና በጉዳዩ ውስጥ ዲፕሎማሲ ሊጫወት የሚችለው ሚና ይኖር እንደሆነ እንዲያብራሩ ለዱያሪች ጥያቄውን ያነሳው ጋዜጠኛ ጠቁሟል።

እስካሁን ከየትኛውም ወገን በይፋ የወጣ መግለጫ የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኢትዮጵያ ወደ ሁለተኛው ሙሌት ብትገባ “ሊገመት የማይችል ትርምስ በአካባቢው ይፈጠራል” ሲሉ የግብፅ ፕሬዚዳንት ባለፈው ሣምንት መዛታቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ግድቡን በመሙላት ካልቀጠለች “ከተቋራጩ ኩባንያ ጋር በገባችው ውል መሠረት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ኪሣራ እንደሚደርስባት” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ አሳውቀው ነበር።

የኅዳሴ ግድብ ግንባታ መሠረት የተጣለበትን አሥረኛ ዓመት አስመልክቶ ከአምስት ቀናት በፊት በትዊተር ገፃቸው ላይ መልዕክት ያሰፈሩት የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ የሆኑት የውኃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ኃይል ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ የግድቡ ግንባታ 79 ከመቶ መጠናቀቁን ገልፀው “ኢትዮጵያ ተፋሰሱን ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በጋራ ለመጠቀም አቋሟ የማይናወፅ ነው” ብለዋል።

XS
SM
MD
LG