በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትግራይ እየተፈፀሙ ናቸው የሚባሉ የጭካኔ አድራጎቶች እንዳሳሰበው የአሜሪካ መንግሥት ገለፀ


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

ትግራይ ክልል ውስጥ እየተፈፀሙ ናቸው በሚባሉ የጭካኔ አድራጎቶች ላይ የሚወጡ ዘገባዎችና የክልሉ ሁኔታ እየተበላሸ መሄድ በብርቱ ያሳሰበው መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትናንት፤ቅዳሜ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “የጭካኔ አድራጎቶች በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል” ሲሉ ባወጡት በዚህ መልዕክታቸው በዛ ባሉ ድርጅቶች ባወጧቸው ሪፖርቶች የጠቆሟቸውን ትግራይ ውስጥ በተለያዩ ወገኖች የሚፈፀሙ ግድያዎችን፣ በግዳጅ ማፈናቀልና የፆታ ጥቃቶችንና የበረቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን እንደሚያወግዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

አድራጎቶቹን የፈፀመ አካልም ተጠያቂ መሆን እንደሚገባቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰብዓዊ እርዳታ ያለ አንዳች መገደብ ለማድረስ፣ ተፈፅመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ምርመራ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአድራጎቶቹን ፈፃሚዎች ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለምአቀፍ ድጋፍን እንደሚቀበል ዓርብ፤ የካቲት 19/2103 ዓ.ም ማሳወቁን መንግሥታቸው እንደሚያደንቅም ሚኒስትር ብሊንከን ገልፀዋል። እነዚህን ቃል የተገባባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በጋራ መሥራት እንደሚገባውም አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን አያይዘውም የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ከትግራይ መውጣት የመጀመሪያዎቹ እጅግ አስፈላጊ እርምጃዎች መሆናቸውን ጠቁመው እርምጃውን ተከትሎም ሁሉም ወገኖች ግጭቱን ለማቆም የየራሳቸውን አዋጅ ማውጣት እንዳለባቸውና ትግራይ ውስጥ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያለገደብ እንዲደርስ መፍቀድ እንደሚኖርባቸውም መግለጫው አሳስበዋል።

ይህንን ግብ ዕውን ለማድረግም ዩናይትድ ስቴትስ ከሌሎች የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ለመሥራትዝግጁ መሆኗንና እርዳታው ፈጥኖ እንዲደርስም የዩናይትስ ስቴትስ ዓለም ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት(ዩኤስኤአይዲ) ወደ ኢትዮጵያ አጣዳፊ የአስቸኳይ ጊዜ ቡድን በመላክ እንደሚሠራ አስታውቋል።

ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር አብረው እንዲሠሩ ለዓለም አቀፍ ሸሪኮች፣ በተለይ ለአፍሪካ ኅብረት፣ በአካባቢው ለሚገኙ አጋሮችና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንተኒ ብሊንከን ጥሪ አቅርበዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ዘላቂ የሆነ አጋርነትን ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኗን ብሊንከንበመልዕክታቸው መጨረሻ አመልክተዋል።

ትግራይ እየተፈፀሙ ናቸው የሚባሉ የጭካኔ አድራጎቶች እንዳሳሰበው የአሜሪካ መንግሥት ገለፀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:31 0:00

(ይህን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል)

XS
SM
MD
LG