በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮሮና ወረርሽኝ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን ህልውና ስጋት ላይ ጥሏል


የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና በየሳምንቱ የሚታተመው የቁምነገር መፅሄት ዋና አዘጋጅ አቶ ታምራት ሀይሉ
የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና በየሳምንቱ የሚታተመው የቁምነገር መፅሄት ዋና አዘጋጅ አቶ ታምራት ሀይሉ

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከጤና ባሻገር የተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ደህንነት ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በወረርሽኙ ምክንያት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መግባቻቸውንና ከመንግስትና ሌሎች ረጂ ድርጅቶች ፈጣን ርዳታ የማያገኙ ከሆነ የተቋማቱ ህልውና ስጋት ላይ እንደሚወድቅ አስታውቀዋል። በዚህም ምክንያት ተቋማቱ ጥምረት ፈጥረው ኢንዱስትሪውን የማዳን ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮና ለሚመለከተው አካል አቅርበዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ድርጅቶች በመቀነሳቸው፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉንና ተቇማቱ የስራ ማስኬጃ የገንዘብ እጥረት እየገጠማቸው በመሆኑ፣ ለሰራተኛ ደሞዝ ካለመክፈል አንስቶ ከገበያ እስከመውጣት የሚያደርስ ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክርቤት የኢትዮጵያ ሲቪክ መረጃ ጥምረት ከተሰኘ የበጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች ስብስብ ጋር በመሆን ባጠናው ጥናት፣ በኮቪድ 19 ምክንያት የመገናኛ ብዙሃን ከማስታወቂያ ገቢ ያገኙ የነበረውን 60 በመቶ ገቢያቸውን ማጣታቸውን አሳይቷል። ጥናቱ፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር ብቻ አንድ የህትመት መገናኛ ብዙሃን ስራውን ለማቆም መገደዱንና ሌላ የቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ ከስርጭት ውጭ መሆኑንም ጥቁሟል።

በዚህ ጉዳይ ያናገራቸው የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤቱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና በየሳምንቱ የሚታተመው የቁምነገር መፅሄት ዋና አዘጋጅ አቶ ታምራት ሀይሉ፣ እርሳቸው የሚመሩት የቁምነገር መፅሄትን ጨምሮ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሚዲያዎች ላይ፣ ለጋዜጠኞች ወረርሽኙን መከላከያ ግብዓቶችን ለማቅረብ አቅም ከማጣት አንስቶ ህትመትና ስርጭትን እስከማስተጏጎል የሚደርሱ ጉልህ ጫናዎች እያሳደረ መሆኑን ያስረዳሉ።

በስሩ 2300 ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኮቪድ 19 ምክንያት ገቢያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ካሽቆለቆሉት የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተቇማት መሃል አንዱ ነው። የድርጅቱ ምክትል ስራ አስፈፃሚና የስልጠናና ጥናት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አቤል አዳሙ እንደገልፁልን፣ በ2006 ዓ.ም. ወደ ኮሮፖሬሽንነት ከተቀየረ በኃላ በአብዛኛው በማስታወቂያ ገቢ የሚተዳደረው ድርጅት የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ያገኝ ከነበረው ጠቅላላ ገቢ 40 በመቶ የሚሆነውን በማጣቱ ትልቅ ጉዳት ደርሶበታል።

ለወራት የአለም ስጋት ሆኖ በቀጠለው የኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በኢትዮጵያ እያሻቀበ መሄዱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን፣ ግለሰቦች ሊያደርጏቸው ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ከማሳወቅ አንስቶ

ኮቪድ-19ኝን የተመለከቱ ወቅታዊ ዘገባዎችን ለማህበረሰቡ የማድረስ ሀላፊነት ተጥሎባቸዋል። ኮቪድ-19 ባሳደረው ተፅእኖ ምክንያት ግን ሀላፊነት የተጣለበት ሚዲያ፣ ህልውናው አደጋ ላይ ወድቇል የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ከመንግስት ድጋፍ እንዲደረግላቸው የመፍትሄ ሀሳብ ያሉትን ጨምረው ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ ታምራት ያስረዳሉ።

በመንግስት የሚነገሩ ማስታወቂያዎች ክፍያን፣ የመንግስትና የግል ሚዲያዎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከመጠየቅ በተጨማሪም የሚዲያ ተቇማቱ ዝቅተኛ ወለድ ያለው ብድር እንዲመቻችላቸው፣ ለመጪዎቹ አምስት ወራት ከሰራተኞች ደሞዝ ላይ የሚቆርጡትን የስራ ገቢ ግብርና የጡረታ መዋጮ መጠቀም እንዲችሉ፣ የአምስት ወር የግብር እፎይታ ግዜ እንዲሰጣቸውና፣ ዓመታዊ የአገልግሎት ክፍያና የህትመት ክፍያን ማዘግየት እንዲችሉም ጠይቀዋል።

የድጋፍ ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ካስገቡ ሶስት ሳምንት እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ታምራት እስካሁን ግን ምንም ምላሽ እንዳላገኙ ይገልፃሉ።

ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ፓርላማ የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በኮቪድ 19 ምክንያት የደረሰበትን ጉዳት አሳውቆ ከመንግስት ድጋፍ ቢደረግለትም ድጋፉ ጊዜአዊ ነው የሚሉት አቶ አቤል፣ የግሉም ሆነ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተለይ በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ካላቸው ትልቅ ሚና አንፃር ማንኛውም ረጂ አካል ሊደግፋቸው ይገባል ይላሉ።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ የቢራ ምርቶች ማስታወቂያ በብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ላይ እንዳይተላለፉ በመደረጉ ና፣ የመንግስት ወጪ ለመቀነስ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ማስታወቂያቸውን በመንግስት ሚዲያዎች ብቻ እንዲነገሩ በመደረጋቸው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እስከ 40 ከመቶ የሚሆነውን ገቢያቸውን ማጣታቸውን የሚገልፁት የሚዲያ ባለሙያዎቹ ኮቪድ 19 ተጨማሪ ማነቆ ሆኖ ህልውናቸውን ሳያጠፋው አስቸኯይ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን ህልውና ስጋት ላይ ጥሏል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:04 0:00


XS
SM
MD
LG