በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የህክምና ባለሙያዎች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል


የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ሠራተኛ
የማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ሠራተኛ

በኢትዮጵያ ህክምና ተቋማት በቂ ራስን ከኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ባለመኖሩና በአጠቃቀም ጉድለት የጤና ተቇማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ለቫይረሱ ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ቪኦኤ ያነጋገራቸው የህክምና ባለሙያዎች ገልፀዋል። የኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በበኩሉ የህክምና ባለሙያዎችን ከወረርሽኙ ለመክላከል የሚያስፈልጉ የህክምና ግብአቶች እጥረት መኖሩን ገልፆ፣ በሚቀጥሉት አንድ ወራት ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራን ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ ለቫይረሱ ተጋላጭ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሄዱንና ይህም ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ያነጋገርናቸው የጤና ባለሙያዎች ገልፀዋል።

የጥቁር አምበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ በህክምና ሙያ የሚያገለግለውና በህክምና ስራው ላይ እንዳለ በኮሮና ቫይረስ በመያዙ በአሁኑ ሰአት በአቃቂ የጤና ጣቢያ ውስጥ ከሌሎች 25 የህክምና ባለሙይዎች ጋር በማገገም ላይ የሚገኘው ዶክተር አብርሃም ገነቱ እንደነገረን፣ በሆስፒታሎች በቂ ራስን መከላከያ ቁሳቁስ ባለመኖሩ በየቀኑ የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱ እየተገኘባቸው ነው።

በቀን ውስጥ እስከ 5 ሺህ ተመላላሽ ታካሚዮችን በሚያስተናግደው የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአሁኑ ሰአት ራሱን ጨምሮ 8 ሀኪሞችና አንድ በልምምድ ላይ ያለ የመጨረሻ አመት የህክምና ተማሪ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የነገረን ዶክተር አብርሃም በተለያየ ጊዜ የኮሮና ቫይረስን መከላከያ ቁሳቁሶች በግዢና በእርዳታ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ ቢነገርም እነዚህ የህክምና ግብአቶች የት እና ለማን እንደሚከፋፈል ምንም መረጃ የለም ያላል።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አድራሮ ወረርሽኙ አለም አቀፍ ከመሆኑ አንፃር የህክምና ግብአቶችን በሚፈለገው መጠን ማግኘት ባለመቻሉ እጥረቱ እንደተፈጠረ ገልፀው ችግሩን ለመቀረፍ ኤጀንሲው 13 ሚሊዮን የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች መግዛቱንና በዚህ ሳምንት አገር ውስጥ ገብቶ መከፋፈል እንደሚጀምር ይገልፃሉ። በመጪው አንድ ወር ውስጥም በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን N95 የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችንና ሙሉ አካል መሸፈኛ ልብሶችን ጨምሮ 160 ሚሊዮን የህክምና ግብአቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡም አቶ ተስፋለም ያስረዳሉ።

የኮቪድ 19 መከላከያ ግብአቶች አቅርቦት መሻሻል ብቻ አሁን ያለውን እጥረት አይፈታም የሚሉት አቶ ተስፋለም የጤና ተቋማት ባለሙያዎቻቸው ቁሳቁሶቹን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከተቇማቱ ያለአግባብ ወጥተው ለብክነት እንዳይዳረጉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳስባሉ።

በየካቲት 12 ሆስፒታል… ስራ ላይ እንዳለ ከሆስፒታሉ ሰራተኞችና ታካሚዎች በተወሰደ ናሙና ክትትል ያደርግላቸው የነበሩ ታካሚ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የሚናገረው ዶክተር አብርሃም፣ ምንም የቫይረሱ ምልክት ሳይኖርባቸው… ለተለያዩ ክትትሎች ወደ ሆስፒታሉ ለሚመጡ ታካሚዎች ያለበቂ መከላከያ የሚያደርጉት እንክብካቤ ‘እኔንና ባልደረባዬን ለቫይረሱ አጋልጦናል’ ይላል።

ሌላው ያናገርነው፣ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀውና በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል አዋላጅ ነርስ ሆኖ የሚያገለግለው የጤና ባለሙያ በሆስፒታሉ 5 የጤና ባለሙያዎችና አንድ የፅዳት ሰራተኛ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኃላ፣ የጤና ባለሙያው ዘንድ ትልቅ መደናገጥ እንደተፈጠረና ያለ በቂ የመከላከያ አቅርቦት ስራቸውን መቀጠላቸው ‘እኔም በቫይረሱ ልያዝ እችላለሁ’ የሚል ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደከተታቸው ይናግራል።

በኢትዮጲያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ የጤና ተቋም ስራተኛች ቁጥር 97 መድረሱንና ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ኖሮአቸው እራሳቸውን ያገለሉ የጤና ባለሙያውች ቁጥር ደግሞ 2340 መድረሱን የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ ባለፈው ሳምንት ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ተናግረው ነበር። በዚህም ምክንያት ከህሙማን ጋር ንክኪ የሚኖራቸው የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን የሚከላከሉበት ዋና ዋና የህክምና ቁሳቁሶችን ለማሟላት፣ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ በወር እስከ 7 ሚሊዮን ድረስ ግብአቶችን የማምረት አቅም ያላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማምረት እንዲጀምሩ እንደሚደረግ አቶ ተስፋለም ጠቁመዋል።

የህክምና ባለሙያዎች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:18 0:00


XS
SM
MD
LG