ድርጊቱ መፈጸሙን ያመኑት የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባም አቶ ተማም ሁሴን መንግሥት ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ከተማውን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመመለስ እየሠራ መሆኑን ከጉዳዩም ጋር በተያያዘ ንብረት በማቃጠልና በተለያየ ወንጀል የተጠረጠሩ 21 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
ነዋሪው እንዲህ አሉ “እኔ ጎረቤቴ ነው የተቃጠለው እንደ አጋጣሚ ሆኖ፣ እኛ ቤት ሲመጡ ለምነናቸው፣ ሳይቀጠል አልፈው ቀጥሎ ያለውን ቤት ነው አቃጥለዋል፡፡ ከኛ ቀጥሎ ያለው ሌላ የቤተሰብ ቤት ተቃጥሏል፡፡ በጣም ብቻ ከባድ ነበር የነበረው ሁኔታው፡፡”
በሁከቱ የወደሙ የንግድ ድርጅቶችን ዘርዝረዋል፡፡
“የአርቲስት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሆቴል፣ በርካታ የንግድ ድርጅቶችን በስሩ ያቀፈው ፀጋዬ ህንጻ፣ ሉሲ የትምህርት ማዕከል አባይ ሆቴል ወሀበ ማራ ህንጻ ሜሪዲያን” እና የመሳሰሉት ተቋማት በእሳት ጋይተው መውደማቸዋን ገልጠዋል፡፡ በዝርዝሩ ከተካተቱ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ በከተማው ትልቁ ነው የተባለው ሉሲ የትምህርት ማዕክል፣ ከነሙሉ ድርጅቱ በቃጠሎው የወደመባቸው መሆኑን የማዕከሉ ባለቤትና ሥራ አኪያጅ አቶ ዮሀንስ ወልዴ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪው ከዘረዘሯቸው ድርጅቶች ውስጥ አቶ ዮሀንስ ወልዴ የሻሸመኔ ነዋሪ ሲሆኑ የሉሲ ትምህርት ማዕከል ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደነገሩን “ሉሲ የትምህርት ማዕከል በከተማው ውስጥ ትልቁና የጀመሪያው የግል ተቋም ነው፡፡ ባሁኑ ሰዐት ወደ 350 የሚደርሱ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ወደ አምስት ቅራንጫፎች አሉት፡፡ በጠቅላላው 4ሺ 200 የሚደርሱ ተማሪዎች በማዕከሉ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡” ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ አገልግሎት የሚሰጠው የዚህ ትምህርት ቤት ይዞታ በሰሞኑ አመጽ የመጋየትና የመውደም አደጋ ደርሶበታል፡፡
አቶ ዮሀንስ በገነቡት የትምህርት ተቋም ላይ የደረሰው አደጋ ግን በዚህ አላበቃም፡፡ ሌላ የሚያሳዝናቸው ነገር ተከተለ፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙት ሰዎች ወደ መኖሪያ ቤታቸውም አምርተዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ መቃጠል የደነገጡት አቶ ዮሀንስ ለህይወታቸውም ስጋት አደረባቸው፡፡ ቤተሰባቸውን ይዘው መኖሪያ ቤታቸውን ትተው ቢያመልጡም መኖሪያ ቤታቸው ግን አላመለጠም፡፡ እግራቸው እንደወጣ የደረሱት ሰዎች ቤታቸውን ከነሙሉ ንብረቱ አነደዱት፡፡
“ከዚያ አልፎ አልፎ በጣምየሚያሳዝነው ቤቴ ድረስ መጥተው፣ ቤቴ መኖሪያ ቤቴ በአጋጣሚ ትምህርት ቤቱ በሚቃጠልበት ሰኣት እኔ ለቅቄ ወጣሁኝ መኖሪያዬን ምክን ያቱም አካሄዱ ከዚህ ሊብስ ይችላል ወደ ህይወቴም ሊመጣ ይችላል በሚል ስጋት ልጆቼን ይዤ ወጣሁኝ ከቤት፡፡ ከዚያ ወዲያው ነው ወደ መኖሬያ ቤቴ የመጡት መኖሪያ ቤቴን እንዳለ አጋዩት፡፡”
አቶ ዮሀንስ ምንም አልቀራቸውም፡፡ የገነቡትን ትምህርት ቤትና መኖሪያ ቤታቸውን አጡ፡፡ እንደዚህ አሉ፤
“እንግዲህ ምንም እሚደረግ ነገር ስለሌለ አሁን እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለናል፡፡”
አቶ ዮሀንስ ወልዴ በትውልዳቸው ከኦሮሞና ከሌላ የተወለዱ ቅይጥ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ በማንነት ተለይቶ የደረሰባቸው ጥቃት ምናልባት የአንድ ወገን አክራሪ ባለመሆናቸው ሊሆን እንደሚችል ገልጠዋል፡፡
አቶ ዮሀንስ ቢያወጡት ቢያወርዱት አልመጣ ያላቸው ነገር ቢኖር የሳቸውም ሆነ ከ22 ዓመታት በላይ የኖረው የትምህርት ማዕከል ጉዳትና ጥፋት ምን እንደሆነ አለማውቃቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የአካባቢውን ማህበረሰብና ተወላጆች ሲያገለግል የኖረን የትምህርት ተቋምን ማውደም ማንን እንደሚጠቅም ባይገባቸውም በትትክል የተረዱት ስሜታቸው ግን የሚከተለው ነበር:-
“በጣም በጣም እጅግ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ በህይወቴ እንዲህ ልቤ የተሰበረበት፣ በአገሬ እምነት ያጣሁበት፣ ሞራሌ በጣም የተነካበት፣ ከምንም በላይ ደግሞ፣ በተለይ ቤት ድረስ፣ በቅድሚያ ሠፈር ውስጥ ካሉት ቤቶች ሁሉ፣ የኔ ቤት ተመርጦ የተቃጠለበት ሁኔታ እግጅ በጣም በጣም አብግኖኛል፡፡ እና በጣም አሳዝኖኛል፡፡ በጣም ሞራሌን ነክቶታል እውነት በኢትዮጵያ በአገራችን ላይ ትልቅ ሀዘን የተሰማኝ ቀን ነው… ይህን ያህል ነው ማለት የምችለው፡፡”
አቶ ዮሀንስን እጅግ የደነቃቸው ነገር፣ በአርቲስት ሀጫሉ ሀዘን ሳቢያ ይህ መሆኑ ነው፡፡ እሳቱን ከለኮሱት በላይ የሀጫሉ ሞት የሳቸው ሀዘን ነበር፡፡ ምክንያቱም ከሀጫሉ ጋር ቤተሰብ ናቸው፡፡ ከባለቤቱ ጋር ዝምድናቸው የሥጋ ነው፡፡ አደጋው ሲደርስ እሳቸው ለአርቲስት ሀጫሉ ለቅሶ፣ ወደ አምቦ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ፡፡
“የባለቤቱ እናት የአክስቴ ልጅ ናት፡፡ ሀዘኑ ከማንም በላይ እሚሰማኝ ነበርና በዚህ ሀዘን ውስጥ ይሄ ነገር መሆኑ ለኔም እንቆቅልሽ ነው ፡፡ እንዲያውም ከአምቦ ደውለው ነው እያጽናኑኝ ያሉት፡፡ የኔንም መጎዳት ሲሰሙ በጣም አዝነው እኔ እነሱን ማጽናናት ሲገባኝ እነሱ እኔ እያጽናኑ ነው ያሉት፡፡”
የአቶ ዮሀንስ ትምህር ቤት በተለይም መኖሪያ ቤታቸው ቀደም ሲል በተያዘ ሊስት ታስቦበት የሳቸው መኖሪያ ቤት ብቻ ተለይቶ የተቃጠለባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“በሁከቱ፣ ያ ሁሉ ንብረት ስለወደመባት፣ የሰው ህይወትና ተስፋ ስለጠፋባት የሻሸመኔን ከተማ፣ ወቅታዊ ሁኔታ ከንቲባው አቶ ተማም ሀሴን የሚሉት ነገር አላቸው፡፡
ነዋሪውም ሆኑ አቶ ዮሀንስ ያሉትን ከንቲባው አላስተባበሉም፡፡ ሰዎች በማንነታቸው ተነጥለው በድርጅቶቻቸውና በመኖሪያ ቤቶቻቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ከንቲባው ተናገረዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም በቁጥጥር ሥር የዋሉ መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡
ከንቲባው “በእንዲህ ያለ ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር ሊከሰት እንደሚችል አልገመታችሁም ነበር? የህብረተሰቡን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ ምን ጥንቃቄ አድርጋችኋል? ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡ ሁሉንም ከምታደምጡት ዘገባ ታገኙታላችሁ፡፡
(ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ይጫኑ)