በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከእራስ አልፎ ለሌላ - በነፃ የቴክኖሎጂ ስልጠና የሚሰጠው ኢትዮጵያዊ


በሎስ አንጀለስ የሚኖረው የቴክኖሎጂ ባለሞያ ዮሴፍ አዱኛ
በሎስ አንጀለስ የሚኖረው የቴክኖሎጂ ባለሞያ ዮሴፍ አዱኛ

በሎስ አንጀለስ የሚኖረው የቴክኖሎጂ ባለሞያ ዮሴፍ አዱኛ ኢትዮጵያውያኖች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ወደፊት ለሚፈጠሩ አዳዲስ የሰራ እድሎች ብቁ ሆነው እንዲገኙ በማሰብ የቴክኖሎጂ ትምህርቶችን በአማርኛ እየተረጎመ ያሰለጥናል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትንም የቴክኖሎጂ ትምህርት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል ያግዛል። ባልደረባችን ስመኝሽ የቆየ ከዮሴፍና እሱ የሚሰጣቸውን የቴክኖሎጂ ትምህርቶች ተምረው ራሳቸውን ከቀየሩ ወጣቶች ጋር ቆይታ አድርጋለች ቀጥሎ ይቀርባል።

ከእራስ አልፎ ለሌላ - በነፃ የቴክኖሎጂ ስልጠና የሚሰጠው ኢትዮጵያዊ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:27 0:00

በዘመናዊው የኢኮኖሚ ውድድር ውስጥ ቴክኖሎጂ ትልቅ ቦታ አለው።የቴክኖሎጂው ዘርፍ እያደገ በሄደ ቁጥር ደግሞ የዓለማችን ኢኮኖሚ በቴክኖሎጂ የታገዝ የሰው ሃይል ይፈልጋል። ይህን መሰርት በማድረግ በሎስ አንጀለስ የሚኖረው የቴክኖሎጂ ባለሙያ ዮሴፍ አዱኛ ኢትዮጵያውያኖች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ወደፊት ለሚፈጠሩ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ብቁ ሆነው እንዲገኙ በማሰብ የቴክኖሎጂ ትምህርቶችን በአማርኛ እየተረጎመ ያሰለጥናል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትንም የቴክኖሎጂ ትምህርት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል ያግዛል።

እስክንድር ብርሃኑ የዛሬ 13 አመት ወደ አሜሪካ ሲመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ የአውቶ መካኒክነት ሙያ ሲማር ከወሰደው የኮምፒውተር ትምህርት በስተቀር ከቴክኖሎጂ ጋር ብዙም ትውውቅ አልነበረውም።

በአሜሪካን አገር ሎስ አንጀለስ ከተማ ኑሮን 'ሀ' በሎ ሲጀምርም የስደት ኑሮውን ለማሸነፍ በመጀመሪያ የተቀጠረው የነዳጅ ማደያ ውስጥ ነበር። ከአመት በኃላ ደግሞ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ታክሲ መንዳት ጀመረ። ለቀጣዮቹ አምስት አመታት ታክሲ እነዳ ነበር የሚለው እስክንድር ራሱንና ኑሮውን ለማሻሻል ትምህርት መማር ቢፈልግም፣ ዮሴፍ አዱኛን እስከሚተዋወቅ ድረስ ግን የቴክኖሎጂ ባለሙያ እሆናለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም።

እስክንድር በ2014 መጨረሻ ላይ የተዋወቀው፣ የያዮቢ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት መስራችና መምህር ዮሴፍ አዱኛ ግን ህይወቴን ቀየረው ይላል። ትምህርት ቤቱ በአማርኛ የሚሰጣቸውን አጫጭር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ለ3 ወራት ስልጠና ከወሰደ በኃላ አሁን ሎስ አንጀለስ ውስጥ ባለ የጤና ድርጅት ውስጥ የሶፍትዌር ዴቨሎፐር ሆኖ ይሰራል።

እስክንድርን ጨምሮ በሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህይወት መቀየር ጀርባ ስሙ ጎልቶ የሚነሳው ዮሴፍ አዱኛ የሶፍትዌር ኢንጅነርና በሎስ አንጀለስ ውስጥ የሚገኘው ሲቲ ናሽናል ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ነው። በዲጂታልና በቴክኖሎጂ ሙያዎች መሰማራት ውጤታማ በሚያደርግበት በዚህ ዘመን ብዙ ከኢትዮጵያ የሚመጡ ወጣቶች በቋንቋ ችግር ምክንያት ከእጅ ወደ አፍ በሆኑ የስራ ሁኔታ ውስጥ ሲንገላቱ ማየት እረፍት ይነሳኝ ነበር የሚለው ዮሴፍ፣ ከ7 አመት በፊት ነበር የቴክኖሎጂ ትምህርቶችን በአማርኛ እየተረጎመ ማስተማር የጀመረው። በአካል ከሚሰጠው ትምህርት በተጨማሪም 20 የተለያዩ በቴክኖሎጂ ዙሪያ ያሉ ኮርሶችን የሚያስተምሩ ከ2 ሺህ በላይ የአማርኛ ቪዲዮዎችን አዘጋጅቶ በድህረ-ገፆች አማካኝነት ለተማሪዎች ያደርሳል።

ዮሴፍ ትውልድና እድገቱ ወሎ ውስጥ፣ ከደሴ 400 ኪሎሜትር እርቀት ላይ የምትገኝ ሳይንት የተባለች የገጠር ከተማ ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ሆቴ እና ወ/ሮ ስህን የተባሉ ትምህርት ቤቶች ተምሮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደሴ ከተማ ያጠናቀቀው ዮሴፍ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተመድቦ እስከምሄድ ድረስ እንኳን ዛሬ በቴክኖሎጂ ሙያ ሌሎችን ላስተምር ለራሴ ምን እንደምሆን አላውቀውም ነበር ይላል።

ዮሴፍ አሜሪካ ከመጣ በኃላ ራሱን በኮምፒውተር ሳይንስና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሙያ ዘርፎች ብቁ ለማድረግ በተከታታይ ለአራት አመታት አምብቧል፣ ከመቶ በላይ አጫጭር ኮርሶችንም ወስዷል። የዛሬ ስድስት አመት ደግሞ እሱ በልፋቱ ያገኛቸውን ስኬቶች ለሌሎች ወገኖቹ ለማካፈል ያዮቢ የተሰኘውን ድርጅቱን ከፍቶ በአማርኛ የሚያዘጋጃቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮርሶች በጣም በትንሽ ክፍያ ያስተምራል። መክፈል የማይችሉትን ደግሞ በነፃ ያስተምራል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ 20 አመት የወሰድኳቸው ኮርሶች ዛሬም በዩንቨርስቲዎች ውስጥ ይሰጣሉ የሚለው ዮሴፍ የትምህርት ተቋማቱ የቴክኖሎጂ ትምህርት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉም በሙያው ድጋፍ ያደርጋል።

አሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ትምህርቶቹን በአካል መስጠት ያልቻለው ዮሴፍ ሰዎች በየቤታቸው ሆነው ከቴክኖሎጂ ትምህርቶች ጋር እንዲተዋወቁ ወይም ያላቸውን እውቀት እንዲያዳብሩ በማሰብ ከ570 በላይ ለሆኑ ተማሪዎች ሶስት ኮርሶችን በነፃ እየሰጠ ነው።

በዚህ እድል ተጠቃሚ ከሆኑ ተማሪዎች መሃል አንዱ ደግሞ በቴኔሲ ስቴት፣ ናሽቪል ከተማ ነዋሪ የሆነው ዚያድ ጀማል ነው። የሂሳብ ባለሙያ የሆነውና በ2010 ወደ አሜሪካ የመጣው ዚያድ፣ ከአንድ ወር በፊት ዮሴፍ በድህረ-ገፅ አማካኝነት የሚሰጣቸውን ሶስቱንም ኮርሶች ጨርሶ መውሰዱ አሁን ለሚሰራው ስራና ወደፊት ለሚኖሩ የስራ እድሎች ብቁ አድርጎኛል ይላል።

ከዚህ በኃላ በቴክኖሎጂ የታገዘ ትውልድ ነው አለም የምትፈልገው፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ ወደ ኃላ ቀርተናል የሚለው ዮሴፍ ጊዜአቸውን ያላግባብ በማህበረሰብ ሚዲያዎች ላይ በቻ የሚያጠፉ ወጣቶች ቴክኖሎጂውን አውቀው ከጊዜው ጋር መራመድ ካልቻሉ ወደፊት ስራ አጥ እንዳይሆኑ ስጋቱን ይገልፃል። በየትኛውም የሙያ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ብቁ እንዲሆኑና እራሳቸውን የዲጂታል ኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲያደርጉም ይመክራል።

XS
SM
MD
LG