በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ኤርትራዊያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዳይገቡ መከልከል አደጋ ላይ ጥሏቸዋል" - ሂዩማን ራይት ወች


ፎቶ ፋይል በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው እንዳባጉና የስደተኞች ጣቢያ ለመግባት በጥር 2016 ዓም ምዝገባ በመጠባበቅ ላይ እያሉ
ፎቶ ፋይል በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው እንዳባጉና የስደተኞች ጣቢያ ለመግባት በጥር 2016 ዓም ምዝገባ በመጠባበቅ ላይ እያሉ

ከኤርትራ ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ድንበር ላይ የሚመዘገቡበትን መስፈርት ኢትዮጵያ መቀየሯ በተለይ እድሜያቸው ለአቅም ያልደረሱ ህፃናትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲል የአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይት ወች ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

"ኤርትራዊያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዳይገቡ መከልከል አደጋ ላይ ጥሏቸዋል" - ሂዩማን ራይት ወች
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:31 0:00

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን ትግራይ፣ህፃፅ ውስጥ የሚገኘውንና ከ26ሺህ በላይ ኤርትራዊ ስደተኞችን የያዘውን መጠለያ ጣቢያ ለመዝጋት መወሰኑንና ስደተኞቹን ወደ ሌሎች ጣቢያዎች እንደሚያዛውር አስታውቋል። በተያያዘም አለምን እያስጨነቀ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙከ700 ሺ በላይ ስደተኞችን ስጋት ላይ ጥሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ወጥተው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ስደተኞችን የአመዘጋገብ ሂደት በድንገት መቀየሯ ኤርትራውያን ስደተኞችን፣ በተለይ ደግሞ ለአቅም ያልደረሱ ህፃናትን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው ሲል የአለም አቅፍ መብት ተሟጋች ድርጅት (ሂዩማን ራይት ወች) ባወጣው መግለጫ ኮንኗል።

በአውሮፓውያን አዲስ አመት መግቢያ፣ ጥር ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ይደረግ የነበረው የአመዘጋገብ ሂደትና የመመዘኛ መስፈርት ግልፅ ባልሆነ መልኩ ቀይሯል፣ በዚህ ምክንያት ደግሞ ለአቅም ያልደረሱ ህፃናትን ጨምሮ የተወሰኑ ኤርትራዊ ስደተኞች አደጋ ላይ ወድቀዋል ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር ለቪኦኤ ገልፀዋል።

"በዚህ ድንገተኛ የአካሄድ ለውጥ ዙሪያ ብዙ ግልፅ ያልሆነ ጥያቄ አለ። ዋናው ችግር ይሄ ለውጥ ሲደረግ ግልፅ ባልሆነ መልኩ መደረጉ፣ እንዲሁም ስደተኞቹ ሲገቡ እርዳታ ከሚሰጧቸው ድርጅቶችም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጥምረት ከሚሰራው የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር ምንም አይነት የማማከር ስራ አለመስራቱ ነው። ስለዚህ ውሳኔው ግራ መጋባትን ፈጥሯል። አገር ውስጥ ያሉና አዲስ የሚገቡ ስደተኞች በአሁኑ ሰዓት ምን ማድረግ እንዳለባቸውና እርዳታ እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው ባለማወቃቸው ትልቅ ፍርሀት ፈጥሮባቸዋል።"

እንደ ሂዩማን ራይት ወች መግለጫ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ኤርትራዊ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ድንበር ላይ ምዝገባ ይደረግላችውና በአካባቢው ወዳሉት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ይላኩ ነበር፣ ጥቂቶቹ ደግሞ ወደ ከተማ እንዲገቡ ይፈቀድላቸው ነበር። ላቲሺያ ድንገተኛ ለውጡ ግን የአለም አቀፉን የስደተኛ አቀባበል ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል።

"በግልፅ የምናሰምርበት ጉዳይ ይሄ ድንገተኛ ለውጥ ኤርትራዊያንን በተለይ ደግሞ እድሜያቸው ለአቅም ያልደረሱ ህፃናትን ጥገኝነት የመጠየቅ መብት የሚገድብ መሆኑን ነው። ይሄ ደግሞ ኢሰብአዊና ኢትዮጵያ እራሷ የፈረመችውን አለም አቀፍ ስምምነት የሚጥስ ነው።"

የኢትዮጵያ መንግስት በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰሜን ትግራይ፣ህጻጽ ይሚገኝውንና 26 ሺህ ኤርትራዊ ስደተኞችን የያዘውን መጠለያ ካምፕ እንደሚዘጋና ስደተኞቹን በአካባቢው ወዳሉ ሌሎች ጣቢያዎች እንደሚያዘዋውር አስታውቇል። ኢትዮጵያ ከዩኤን ኤች ሲ አር በአመት ታገኝ የነበረው በጀትም በዘንድሮው አመት እጅጉን ቀንሷል። ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የ ዩ ኤን ኤች ሲ አር ቃልአቀባይ ክሱት ገብረእግዚአብሄር፣ የካምፑን መዘጋት አስመልክቶ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልፀው፣ የኢትዮጵያ በጀት ለምን እንደተቀነሰ ግን ነግረውናል።

“በጀቱን በተመለከት ዩ ኤን ኤች ሲ አር ከተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች ከሚመደብለት 2 ፐርሰንት በስተቀር፣ ከረጂ አካላት በየአመቱ እየሰበሰበ ነው እስካሁን የሚሰራው። ገቢ የማሰባሰብ ጉዳይ ቀላል አይደለም። በአለማችን ደግሞ ቀውሶች በበዙ ቁጥር፣ በተለይ ወሳኝ የሚባሉ ረጂዎች ተመሳሳይ ስለሆነ አቅማቸው ይከፋፈላል። ዩ ኤን ኤች ሲ አር ባገኘነው መሰረት ነው የሚመድበው፣ ስለዚህ እጥረት አለ።”

በተያያዘ፣ የኮሮና በሽታ ወደ ሀገር ውስጥ መግባትን ተከትሎ በኢትዮጵያ ተጠልለው የሚገኙ ወደ 800 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ለአደጋ ተጋልጠዋል። ይህን ተከትሎ ዩ ኤን አኤች ሲ አር ከመንግስት ጋር በመተባበር ስደትኞች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰራ ቢሆንም ቃል አቀባዩ ክሱት ገና ብዙ የሚቀር ነገር እንዳለ ያስረዳሉ።

“እንግዲህ እያንዳንዱ የስደተኛ ካምፖች ላይ የጤና ጣቢያ አለ። እነዚህ ግን መሰረታዊ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው እንጂ እንደዚህ አይነት ውስብስብ የሆነ አደጋ በሚያጋጥም ጊዜ በሙሉ አቅም መከላከል የሚያስችል አቅም ያላቸው አይደሉም። በሰው ሀይልም ጭምር ቢሆን ለእንደዚህ አይነት ሁኔታ በደንብ የተደራጁ አይደሉም። ስለዚህ እሱ አንድ ችግር ሆኖ፣ እዛ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችም የግል ደህንነታቸውን የሚጠብቁበት የኢንፌክሽን መከላከያ ግብአቶች እጥረቶችም አሉባቸው። ጊዜ የማይሰጥ ነገር ስለሆነ በተቻለ መጠን እዚሁ አገር ውስጥ የተግኙ ነገሮችን ለመግዛት ጥረት እየተደረገ ነው ያለው። ነገር ግን በጥቂቱ የሚበቃ ስላልሆነ ቢያንስ ለእያንዳንዱ ከጤና ጋር የተያያዘ ስራ ለሚሰሩት የኢንፌክሽን መከላከያ ግብአቶች እንዲኖርና የጤና ጣቢያዎችም በተቻለ መጠን እንዲደራጁ መደረግ አለበት። እሱ አንድ ችግር ነው።

እነዚህንና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲያብራሩልን የደወልንላቸው የስደተኞችና የስደት ተመላሾች ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ በጉዳዩ ላይ ማውራት አልችልም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ምክትል ዳይሬክተሩን እዮብ አወቀን በስልክ ለማግኘት ያረግነው ጥረትም አልተሳካም።ምላሻቸውን እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።

XS
SM
MD
LG