ላለፉት 8 አመታት በፎቶ ጋዜጠኝነት ሙያ ያገለገለው ሙሉጌታ አየነ ለዘንድሮው የዓለም አቀፍ ሽልማት የዓመቱ ፎቶ፣ የአመቱ የፎቶ ታሪክ እና የዋና ዜና ታሪክ ምድቦች ታጭቶ የነበረ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ በዋና ዜና ታሪክ ስብስብ ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል። አሸናፊ የሆነበት ፎቶ አለም አቀፉ የዜና ወኪል ።። ውኪል የሆነላቸው በመላው አለም የሚገኙ ታላላቅ የመገናኛ ብዙሀን ተቇማት በፊት ገፆቻቸው ላይ ተጠቅመውታል። በወቅቱም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በከፍተኛ ቁጥር የተጋራ ፎቶ ነበረ። ሙሉጌታ ሽልማቱን በማግኘቱ የተሰማውን ለቪኦኤ ሲገልፅ፣
“በማሸነፌ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ይሄ ድል የኔ ብቻ አይደለም። የመላው አፍሪካዊ ወጣት ፎቶ አንሺዎች በፎቶ ጋዜጠኝነት ላይ መስራት እንዳለባቸው ይሰማኛል። አፍሪካውያን የራሳችንን፣ አገራችን ላይ የሚፈጠረውን ነገር በራሳችን አለም ላይ ማሳየት ይኖርብናል። ወጣት የአፍሪካ ፎቶ አንሺዎችንም የሚያነሳሳ ነው ብዬ ነው የማስበው።”
ሙሉጌታ ያሸነፈበት የዛሬ አመት ቢሾፍቱ አቅራቢያ በወደቀው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አይሮፕላን አደጋ ለሞቱ ቤተሰቦቻቸው ፊታቸው ላይ አፈር እየበተኑ ሲያለቅሱ የሚያሳየው ፎቶ እጅግ ስሜቱን የነካው ፎቶ እንደሆነ ይናግራል።
ለኔ እጅግ በጣም ስሜቴን የነካኝ ስራ ነው ምክንያቱም እጅግ በጣም ነው የሚያሳዝነው። ቤተሰቦቻቸውን፣ ልጃቸውን፣ ሚስታቸውን፣ ጏደኞቻቸውን ያጡ ቤተሰቦች መጥተው ሀዘናቸውን ሲገልፁ የሚያሳዩ ፎቶዎች ናቸው። እጅግ ልብ የሚነካና ጭንቀት ውስጥ ከቶኝ የነበረ ስራ ነው። በጠቅላላ የነበረው ነገር ስሜታዊ የሚያድርግ ነበር። በዛ ፎቶ ነው ማሸነፍ የቻልኩት። "
አደጋው በደረሰበት ወቅት ለሰባት በተከታታይ ቀን አደጋው የደረሰበት ቦታ ለሊት በመሄድ ቀኑን ሙሉ ያሳልፍ እንደነበር ገልፆ ፎቶውን ለውድድር ብሎ ባያነሳውም ፎቶው በአለም አቀፍ ውድድር ላይ ማሸነፍ መቻሉ ግን እንዳስደሰተው ይገልፃል። ያገኘው ሽልማት የውድድር ሁሉ ቁንጮ ነው የሚለው ሙሉጌታ ሌሎች በሙያው ያሉ የፎቶ ጋዜጠኞችንና ወደሙያው መምጣት የሚፈልጉ ወጣቶችን ያበረታታል ብሎ ያምናል።
(በድምፅ ለመስማት የተያያዘውን ፋይል ይክፈቱ)