በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአራት ልጆች እናቷ ኢትዮጵያዊት አራስ ስንብት - በቨርጂኒያ መቃብር ቦታ


“እርሷ ለልጆቿ ሕይወቷን እንደሰጠች እኔም እሰጥላታለሁ። ልጆቹን ሰብስቤ አሳድግላታለሁ” - የ17 ዓመቷ የወገኔ ልጅ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ማስጨነቅ ከጀመረ፣ ሥርጭቱን ለመግታትም አካላዊ መራራቅ ተግባራዊ በተደረግባት ዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች በኮሮናቫይረስም ይሁን በሌላ ሕመም ሕይወታቸው ሲያልፍ የሚወዷቸውን ሰዎች በመቃብር ቦታ ተገኝተው እንዲሰናበቱ የሚፈቀደው ለአምስት ወይም ዐስር ሰዎች ብቻ ነው።

ለወትሮው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ሰው ሲሞትባቸው እንደየ እምነታቸው በአዳራሽ ወይም በቤተ እምነቶቻችቸው የስንብት ዝግጅት አሰናድተው ሲጨርሱ ነበር ወደ ቀብር ቦታው የሚወሰዱት። የቀብር ሥነ- ስርዓቱ ሲከናወንም በመቃብሩ ቦታ በጣም በዛ ያሉ ሰዎች በቤተክርስቲያን መሪዎቻቸው ታጅበው ነበር ለሽኝት የሚሄዱት። አርብ ሚያዚያ 16/ 2012 ዓ.ም በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የቀብር ሥነ- ስርዓታቸው በተፈፀመው በአራት ልጆች እናት ወ/ሮ ወገኔ ደበሌ ስንብት ግን የተገኙት ሰዎች ቤተሰብን እና የቀብር አፈፃሚዎቹን ጨምሮ ከ15 አይበልጡም።

የወ/ሮ ወገኔ ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት በጥቂት ሰዎች ሲከናወን
የወ/ሮ ወገኔ ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት በጥቂት ሰዎች ሲከናወን

አፍና አፍንጫቸውን በመሸፈኛ ማስክ በከለሉ ጥቂት ሰዎች ብቻ በተከናወነው በዚህ የቀብር ሥነ ስርዓት በተራራቁ ሰዎች መካከል ከልጃቸው ጋር ብቻ ተጠጋግተው ሐዘናቸውን የሚገልፅጹት አቶ ይልማ አስፋውም ሆነ ልጃቸው ምሕረትን እንደ ኢዮጵያውያን ባህል መሰረት ደግፎ የሚያፅናናቸው ሰው አልነበረም። ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክኒያት እንዳይጠጋጉ በመከልከሉም አንዴ በሳጥኑ ስር እየተቀመጡ፣ እየተቃቀፉና እያለቀሱ በተስፋ መቁርጥ ስሜት የሚያነቡን አባትና ልጅ ራቅ ብሎ ቆሞ መመልከት የሚፈጥረው የውስጥ ሕመም ከባድ መሆኑንም ለማፅናናት በቦታው ከተገኙትን ጥቂት ሰዎች ፊት ላይ በቀላሉ ማስተዋል ይቻል ነበር።

በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የወ/ሮ ወገን ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት ሲፈፀም ባለቤታቸው አቶ ይልማ አስፋውና የ17 ዓመት ልጃቸው አቶ ይልማ አስፋው
በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የወ/ሮ ወገን ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት ሲፈፀም ባለቤታቸው አቶ ይልማ አስፋውና የ17 ዓመት ልጃቸው አቶ ይልማ አስፋው

ከጥቂቶቹ ቀባሪዎች አንዱ ሆነው በዚያ የተገኙት ሲልቨር ስፕሪንግ ከሚገኘው የቤተሰቡ የማምለኪያ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ- ክርስቲያናቸው የመጡ አንድ ወንጌላዊ ራቅ ብለው ያደረጉት የአጭር ደቂቃ ስብከትም በማፅናኛ ቃል የተሞሉ ነበሩ።

የ43 ዓመቷ ወ/ሮ ወገኔ ደበሌ እና ባለቤቷ የ50 ዓመቱ አቶ ይልማ አስፋው፤ አሁን የ17 ዓመት ልጅ የሆነችውን ምህረት እና የዐሥር ዓመት ልጅ የሆነውን ናኦልን ይዘው ነበር ከዐሥር ዓመት በፊት በዲቪ ሎተሪ ከኢትዮጵያ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጡት። አቶ ይልማ በሞንጎመሪ ካውንቲ ውስጥ የትምሕርት ቤት አውቶብስ አሽከርካሪ ናቸው። በኢትዮጵያ በአንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ ላብራቶሪ ቴክኒሺያን የነበሩት ወ/ሮ ወገኔ አንድ ጊዜ በመሥራት ሌላ ጊዜ ደግሞ በቤት ውስጥ ልጆች በማሳደግ ነው ያሳለፉት።

ወ/ሮ ወገኔ አሁን ከተወለደ ሦስት ሳምንት የሆነውን አራስ ልጃቸውን የስምንት ወር ነፍሰጡር እያሉ መጋቢት 10 /2012 ዓ.ም ሆሊክሮስ ወደሚገኘው መደበኛ ሃኪማቸው ጋር ለክትትል ሲሄዱ ትኩሳት ስላላቸው ወደ ድንገተኛ ክፍል ተመርተው ነበር። ባለቤቷ አቶ ይልማ እንደነገሩን ራሳቸውን ብቻ እንዲንከባከቡ ነግረው መለሷቸው። እቤት ከመጡ በኋላ ሁኔታው እየባሰባቸው ሲሄድ ከአምስት ቀን በኋላ መጋቢት 16 ወደ ሆስፒታል መለሷቸው።

በወቅቱ የመተንፈስ ችግር ያጋጠቸው በመሆኑም ልጃቸው ሌቪንን እንዲወለድ ተደረገ። ባለቤቷና ልጆቿ ወገኔን ከዚያ በኋላ መልሰው አላዩዋቸውም። በኮሮናቫይረስ ምክኒያት በደረሰባቸው ሕመም ለከፍተኛ ሕክምና በተዘዋወሩበት ሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ሚያዚያ 13/2012 ዓ.ም የወለዱትን ልጅ የማየት ዕድል ሳያገኙ ሕይወታቸው አልፏል።

በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የወ/ሮ ወገን ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት ሲፈፀም ባለቤታቸው አቶ ይልማ አስፋውና የ17 ዓመት ልጃቸው አቶ ይልማ አስፋው
በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የወ/ሮ ወገን ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት ሲፈፀም ባለቤታቸው አቶ ይልማ አስፋውና የ17 ዓመት ልጃቸው አቶ ይልማ አስፋው

“እናቴን የመሰናበት ዕድል እንኳን አልነበረኝም” ትላለች የ17 ዓመቷ ልጇ ምሕረት ይልማ ወደ ሆስፒታል ስትገባ አንዴ ደውላላት የተባለችውን ከነገረቻት በኋላ መልሳ ድምጿን እንዳልሰማችው በሐዘን ትገልፃለች። “እርሷ ባታየንም ባትሰማንም አንድ ግዜ “ዙም” በተሰኘ የኢንተርኔት ላይ መደወያ እንዳየቻት ትናገራለች።

ምህረት የእናቷን ሳጥን ያለበት አስክሬን አንገቷን ሰብር አድርጋ በሰቀቀን ታለቅሳለች “ አንድ ሰው አይደለም ያጣሁት ሦስት ነው።እናቴን እህቴን እህቴን ...ጓደኛዬ” ትላለች። “ሴት ልጇ እኔ ብቻ ስለነበርኩ በጣም እንቀራረብ ነበር። እናቴ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ሩጫዬን ጨርሻለሁ” በሚል በተፃፈው መሰረት ሩጫዋን ጨርሳ ወደ ፈጣሪዋ ወደ አባቷ እንደሄደች አምናለሁ። ይህንን እምነት እና ጥንካሬን ያስተማረችኝ እርሷ ናት።እዚህ የደረስኩትም በእርሷ ነው። ግን ቻው እንኳን ሳልላት ነው የሄደችው። ልጇን እንኳን አላየችውም።” ብላናለች።

በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የወሮ ወገን ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት ሲፈፀም ባለቤቷ አቶ ይልማ አስፋውና ወዳጆቻቸው
በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የወሮ ወገን ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት ሲፈፀም ባለቤቷ አቶ ይልማ አስፋውና ወዳጆቻቸው

አባቷ አቶ ይልማ፤ “ሕፃኑን የያዘችው እርሷ ናት ወተት እየበጠበጠች ታጠባዋለች፤ምክኒያቱም ከውጪ ሰው አይገባም። በዛ ላይ ልጆቹም ምናልባት በቫይረሱ እንዳይጠቁ ለጥንቃቄ ሲባል ማንም አይጠጋቸውም። እንደገና ደግሞ እኔ ከዱሮ ጀምሮ አራስ ልጅ መያዝ አልችልም” ብሎን ነበር። እርሷም እንደነገረችን የተወለደውን አራስ ልጅ መያዝ ከጀመረች ሦስት ሳምንቷ ነው።

"የተወለደውን ሕፃን ሳይ እናቴን ያሳታውሰኛል። ልጆቹን ሳይ እሷን ያገኘኋት ይመስለኛል። ከእንግዲህ በኋላ እነሱ ናቸው ያሉን። እሷ ‘አንቺ ስትወልጂ ልጅ የሚጠብቅልሽ ሰው አያስፈልግሽም እኔ ነኝ የማሳድግልሽ’ ትለኝ ነበር። እርሷ ለልጆቿ ህይወቷን እንደሰጠች እኔም እሰጥላታለሁ። ልጆቹን ሰብስቤ አሳድግላታለሁ”


የ17 ሰባት ዓመቷ ምሕረት በወላጅ እናቷ ቀብር ላይ የገባችው ቃል ነው።

ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ እንደሚገኝበት ይገመታል። የወ/ሮ ወገኔ ሕይወት ማለፍና የቤተሰቡ ሁኔታ ሲሰማ፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ወዲውኑ ነው ቤተሰቡን በገንዘብ ለማገዝ የጎ ፈንድ ሚ ገፅ የከፈቱት። ለአገር ውስጥ የቴሌቭዥን አገልግሎት WSA9 አስተያየት የሰጡት የታኮማ ፓርክ ከንቲባ ኬት ስትዋርት፣ “የታኮማ ማኅበረሰብ ቤተሰቡን መርዳት መቀጠል ይፈልጋል” ቤተሰቡም የኛን ድጋፍ ይፈልጋል ብለዋል።

ከቀብር አስፈፃሚዎቹ አንዱ ጀሚስ ክሊክ፤ ኮረና ቫይረስ ሰዎች የሚወዷቸውን ሰዎች ለመሸኘት ያደርጉት የነበረውን ባህላዊ ስርዓት እንዳያከናውኑ ከልክሏቸዋል ይላሉ።“ለወትሮው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ወደ ቀብር ቦታ ሲመጡ በእምነት አባቶቻቸው ታጅበው፣ ሻማ እና የመሳሰሉትን ነገር ይዘው በዛ ብለው ነበር የሚመጡት አሁን ግን ያው እንደምታዩት ልክ እንደ ዛሬው ጥቂት ሰዎች ሆነው ይመጣሉ ወይም ደግሞ በስልክ ያስፈፅማሉ” ሲሉም ከዚህ ቀደም ያዩትን ያስታውሳሉ።

ፀገነት በቀለ የእነ ወ/ሮ ወገኔ ጎረቤት ናቸው፤ “ ከኢትዮጵያ ከመጣች ጀምሮ አብረን አንድ ፎቅ ላይ ነው የምንኖረው። እኔ ሶስተኛ ፎቅ ነኝ እርሷ ስምንተኛ ፎቅ ናት። በጣም ሰው የምትወደ ሰው ነበረች። አራስ ሆና በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ህይወቷ ማለፉ እግጅ በጣም ያማል። በዛ ላይ እኛ በባህላችን ሰው ሲሞትብን ሰው ተሰብስቦ ደጋግመን አልቀሰን እርስ በእርስ ተፅናንተን ነው የሚወጣል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አልቅሶ እንኳን ሐዘን በማይወጣበት ሁኔታ መሆኑ እጅግ በጣም ያሳዝናል።” ካለች በኋላ አያይዛ “ወገኔ በሰዎች ዘንድ የምትታወቀው የልጆቿ ወታደር በሚል ነው። ልጆቿን ትዳሯን በጣም ትወዳለች። ሰዎ በጣም ይወዳታል። ማንኛውም ሰው ዝግጅት ሲኖረው አትቀርም አድማቂ ነበረች ከጎረቤቶቿ ጋር በጥሩ የምትገባባና ሰው የምትቀርብ ሰው ነበረች” ትላለች ሲቃ በያዘው የሐዘን ድምፅ።

በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የወሮ ወገን ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት ሲፈፀም ባለቤቷ አቶ ይልማ አስፋውና ወዳጆቻቸው
በቨርጂኒያ ዊልክስ ጎዳና በሚገኘው የመቃብር ቦታ የወሮ ወገን ደበሌ የቀብር ሥነ ስርዓት ሲፈፀም ባለቤቷ አቶ ይልማ አስፋውና ወዳጆቻቸው

ከወገኔ ጋር በጓደኝነትም በትዳርም ወደ 25 ዓመታችን ነው። የልጅነት ጓደኛዬ የልጅነት የትዳር አጋሬ ነበረች። ወገኔ ለልጆቿ እናት ብቻ አልነበረችም” ያሉን ባለቤቷ አቶ ይልማ በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት የማሳረጊያ ንግግርም፤ “ወገኔ በማኅበረሰቡ በጣም የተወደደች ስለነበረች በሆስፒታል በነበረችበት ጊዜ ሁሉ የታኮማ ነዋሪዎች በሙሉ በጣም ጥሩ ድጋፍ አድርገውልኛል። የታኮማ ካውንስሉም ሐዘናቸውን ከመግለፅ ጀምሮ በጣም ጥሩ ድጋፍ አድርገውልናል እናመሰግናለን። ጎፈንድሚ ከፍተው ትልቅ ትብብር ያደረጉልኝን በጣም አመሰግናለሁ። ዘር ቀለም ክርስቲያን ሙስሊም ለልጆቹ ብሎ እርዳታ ላሰባሰበልን ሁሉ በጣም እናመሰግናለን።” ብለዋል።

ባለቤቷ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ማዳማጥ ይቻላል።

የወለደችውን ልጅ ሳታይ ኢትዮጵያዊቷ በኮሮናቫይረስ ሕይወቷ አለፈ
please wait

No media source currently available

0:00 0:16:37 0:00


(ዘገባው የጽዮን ግርማ ነው)

XS
SM
MD
LG