በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ውሎ


VOA
VOA

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች የተለያዩ ከተሞች ጥቃት በፈፀሙ ታጣቂ ኃይሎች ላይ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታወቀ።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ውሎ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:27 0:00

የጽሕፈት ቤቱ ፕሬስ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከመጋቢት 24/2011 ዓ.ም ጀምሮ ከሚሴ ላይ የተጫረውንና ወደ አጣዬ፣ ካራ ቆሬ፣ ማጀቴና ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ተዛምቶ የነበረውን ግጭት በተመለከተ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አካባቢውን ለማረጋጋትና ነዋሪዎቹን ለመታደግ ተመጣጣኝ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ለፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላት ትዕዛዝ መተላለፉን አረጋግጠዋል።

በተወሰዱት እርምጃዎች ምክንያት የከትናንት በስተያው ቅዳሜ ከፍተኛ ችግር ተስተውሎባቸው የነበሩት ኬሚሲ፣ አጣዬ እና ማጀቴ መረጋጋት እንደታየባቸው አቶ ንጉሡ ገልፀዋል።

በአካባቢው በተከሰተው ግጭትና በተፈፀመው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን፣ ሕይወት መጥፋቱን፣ በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንና ንብረት መውደሙን የክልሎቹ መንግሥታት፣ የመከላከያ ሚኒስቴርና የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ቢያረጋግጡም እስካሁን የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት በተመለከተ “ተጣርቶ ይቀርባል” ከሚል ውጪ በይፋ የተገለፀ ነገር የለም።

ግጭቱ በጦር መሣሪያና በከፍተኛ ተኩስ የታጀበ እንደነበር ሁሉም ወገን ቢያረጋግጥም ማን እንደጀመረው? እንዴት እንደተጀመረና የታጠቀው አካል ማን እንደነበር እርስ በእርስ ከመወነጃጀል ውጭ የታወቀ ነገር የለም።

የመጀመሪያው ግጭት በተጫረበት በወሎ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ ሐሰን ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) መጋቢት 27/2011 ዓ.ም. ከሚሴ ላይ ስብሰባ ለማካሄድ ጠይቆ እንደነበር ገልፀው ነገር ግን በአካባቢው ያለውን የወቅቱን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ አስተዳደሩ ፍቃድ መንፈጉን አመልክተዋል። ይህንን ተከትሎም በተፈጠረ አለመግባባት የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ ተኩስ መክፈቱን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገደቢ ኃይሉ በሰጡት ቃል “ከነፍስ ወከፍ ትጥቅ ከፍ ባለ ሁኔታ በሚገባ የተደራጀና የጦር መሣሪያ የታጠቀ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሠራዊት ተኩስ ከፍቶ ከፍተኛ ጥቃት ፈፅሟል” ብለዋል።

በሌላ በኩል ግን ኦነግ በሰጠው ምላሽ “እንዲህ ዓይነት ክሦች ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሠሩ እንጂ "የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ምንም ዓይነት የታጠቀ ኃይል በዚያ አካባቢ የለውም" ሲሉ የግንባሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቶሌራ አደባ ተናግረዋል።

ይህን ግጭት በማነሳሳት እጁ አለበት በሚል ክስ የቀረበበት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚና የጥናትና ስትራተጂ ክፍል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ኢብራሂም፤ “ፓርቲያችን በዚህ ግጭት እጁ የለበትም፤ እኛ የራሳችን ሰንደቅ ዓላማም ሆነ የጦር መሣሪያ የሌለን ሰላማዊ ፓርቲ ነን” ብለዋል።

ከዚህ ይልቅ አካባቢው ላይ ሥጋት መኖሩን በማየት ለአማራ ክልል ጥቆማ መስጠታቸውንና ጥቆማውን ተከትሎ አስቀድሞ ምንም ዓይነት መከላከል ባለመደረጉ ክልሉን ወቅሰዋል።

በሌላ በኩል በትናንትናው ምሽት በአሜሪካ ድምፅ የተጠየቁት የሃገሪቱ ጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ተስፋዬ አያሌው፤ ‹‹ግጭቱ የተከሰተው በሕዝቦች መካከል አይደለም፤ የተጋጩትና የተታኮሱት በሁለቱም በኩል ያሉ ታጣቂዎች ናቸው›› ብለዋል። በግጭቱም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል

አርብቶ አደር ይበዛበታል ባሉት በዚሁ አካባቢ አብዛኛው ሰው ባለመሣሪያ መሆኑን የጠቆሙት የምክትል ኤታማዦር ሹሙ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ “ኦነግ በአካባቢው የታጠቀ ኃይል የለውም፤ ነገር ግን እዛ አካባቢ ሕዋስ የላቸውም ወይም እነሱን የሚደግፍ የለም ብሎ መናገር አይቻልም” ሲሉ አክለዋል።

መንግሥት የመከላከያ ሠራዊቱን ወደ አካባቢው ካሠማራ በኋላ ተኩስ መቆሙን የተናገሩት ኮሎኔል ተስፋዬ ግጭቱ እንዴት እንዴት፣ የት፣ በማን እንደተነሣ፤ ያባባሰው ማን እንደሆነና የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ማጣራት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሎኔል ተስፋዬ ዛሬ መግለጫ እንደሚሰጡ ገልፀውልን የነበረ በመሆኑ ሁኔታውን ለመከታተል የእጃቸው ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።

በተመሳሳይ በዛሬውን ላይ መረጃ ለማግኘት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅሕፈት ቤት የፕሬስ ኃላፊ ወደ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የእጅ ስልክም ደውለን ነበር፤ አላገኘናቸውም።

በሌላ በኩል ማምሻውን በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ)፤ “ጽንፈኛ የፖለቲካ ሃይሎች የከሰሩ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ለዘመናት በአብሮነት እና በፍቅር የኖረን ሕዝብ ሊያቃቅሩ ብሎም ሊያጋጩ የሚችሉ አጀንዳዎቸን በመቅረጽ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨትና ንፁሃን ዜጎችን በእሳት በመማገድ ሀገራችን ከማትወጣበት የግጭት አዙሪት ዉስጥ በመክተት የለዉጥ እንቅስቃሴዉን ማደናቀፍ ዋነኛ አላማቸዉ አድርገዉ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡” ብሏል።

ፓርቴው የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት እና ተመሳሳይ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል ከአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና ከአማራ ክልላዊ መንግስት ጋር በመቀናጀት በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በተጨማሪም የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ማምሻውን ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች የአዴፓ እና የአማራ ሕዝብ አንድነት የሚያስፈራቸው ኃይሎች የፈጠሩት ሴራ ነው” በማለትም ተናግረዋል፡፡

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG