በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ያልተፈቱ እስረኞች እንዲለቀቁ ጠበቆችና ቤተሰቦች እየጠየቁ ናቸው


የኦነግ ወይም የግንቦት ሰባት አባል ናቸው በሚል የሽብር ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ተከሳሾች ከሌሎቹ ተነጥለው ከእስር አለመፈታታቸው እንዳስከፋቸው ከእስረኛ ቤተሰቦች የተወሰኑት ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ያልተፈቱ እስረኞች እንዲለቀቁ ጠበቆችና ቤተሰቦች እየጠየቁ ናቸው
please wait

No media source currently available

0:00 0:21:12 0:00

የኦነግ ወይም የግንቦት ሰባት አባል ናቸው በሚል የሽብር ክስ ቀርቦባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ተከሳሾች ከሌሎቹ ተነጥለው ከእስር አለመፈታታቸው እንዳስከፋቸው ከእስረኛ ቤተሰቦች የተወሰኑት ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ቁጥራቸው በርከት ያለ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ ደንበኞች ያሏቸው “አራት” ጠበቆች በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የገባውን እስረኞች የመፍታት ቃል እንዲያከበር ጠይቀዋል። በአንድ ዓይነት ክስና በተመሳሳይ የክስ መዘገብ የተከሰሱ እስረኞችን ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ ከእስር እንዲለቃቸው ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የእስረኛ ቤተሰቦች አቤቱታ

ማስተዋል ግዛቸው በሽብር ወንጀል ተከሶ በእስር ላይ የሚገኘው ወጣት ዮናስ ጋሻው እህት ናት። “ወንድሜ ነው። የእናቴ ልጅ። አብረን እየሄደን ነበር ሳሪስ አካባቢ የታሰረው” ትላለች በታኅሣሥ ወር 2008 ዓ.ም የታሰረበትን ሁኔታ አስታውሳ ።

በእስር ላይ እያለ በደረሰበት ድብደባና ማሰቃየት አንድ እግሩ መጎዳቱን ትናገራለች። በሁለት እግሮቹ ለመራመድ ስለማይችል የሚታገዝበት የብረት መራመጃ እደሚያስፈልገውም ገልፃለች። አያይዛም“የተሟላ ምግብ አያገኝም፣ ሕክምና ተከልክሏል፣ መታጠቢያ ቤት ብቻውን መንቀሳቀስ አይችልም። እኔ ለማን አቤት እንደምልና የት ሄጄ እንደማመለክትም ግራ ገብቶኛ” ትላለች።

መንግሥት እስረኞችን እንደሚፈታ ከገለፀ በኋላ ወንድሟ ይፈታል ብላ በጉጉት ብትጠብቅም ሌሎች እስረኞች ሲፈቱ የእርሱ አለመፈታተ ግራ እንዳጋባት ትገልፃለች። “ከዛ ውስጥ በሕይወት ወጥቶ ሕክምና እንዲያገኝ ብቻ ነው የምለምነው” ስትል ማስተዋል ተማፅኖዋን ለመንግሥት ታቀርባለች።

አቶ ሲያምር ጌቴ በእስር ላይ የሚገኘው መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የአክስት ልጅ እንደሆነ ገልፆልኛል። መንግሥት በሽብር ወንጀል የተከሰሱ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ሲጀምርና በመቶ አለቃ ማስረሻ መዝገብ የተከሰሱ ተከሳሾች ሲለቀቁ የእርሱ ዘመድም ከእስር ይለቀቃል የሚል ተስፋ እንደነበረው ይናገራል።

“ነገር ግን ደካማ እናትና አባቱን ጨመሮ ቤተሰቦቹ እንደጠበቁት ሳይፈታ ሲቀር ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሙሉ አመልክተናል። እስካሁን ግን ምንም ምላሽ አላገኘንም ”ይላል።

ሌሎቹ እስረኞች እንደተፈቱት ሁሉ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤም ከእስር ይለቀቅ ይሆናል በሚል ተስፋ እየጠበቁ መሆኑን ይናገራል።

አቶ ፍትሕዓለው ተሰማ በእስር ላይ የሚገኘው የሌላኛው እስረኛ አቶ አስቻለው ደሴ የአክስት ልጅ ነው እርሱም እንደሌሎቹ እስረኛ ቤተሰቦች የዘመዱን የመፈታት ዜና በተስፋ ሲጠባበቅ እንደነበር ይናገራል። “በተለይ በእስር ላይ እያለ በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ምክኒያት ብልቱ ላይ አደጋ ደርሶበታል። በእስር ላይ እያለ ሕክምና አላገኘም። ሌሎቹ አብረውት የተከሰሱት ከእስር ሲፈቱ እርሱም ተለቆ ሕክምና ያገኛል የሚል እምነት ነበረን አሁንም የምንጠብቀው ይህንኑ ነው” ብሏል።

ሌላው በእስር ላይ የሚገኘውና አባቱ አቶ አስማማው ዋለልኝ ከእስር ይለቀቃል የሚል ተስፋ የነበራቸው እስረኛ አቶ ፍቅረማሪያም አስማማው ነው። ፍቅረማሪያም የሰማያዊው ፓርቲ አባል የነበረና “ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀል ነበር” በሚል የታሰረ ነው። ከእርሱ ጋራ በተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ ሌሎች ተከሳሾች ከእስር ተለቀዋል።

አባቱ አቶ አስማማው የልጃቸውን የፍርድ ሂደት በትኩረት መከታተላቸውን ገልፀው የቀረበበት ማስረጃ ስለሌ መጀመሪያ ሊታሰር አይገባውም ነበር በሚል ይከራከራሉ። ከታሰረም በኋላ ደግሞ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ መሰረት ከእስር ሊፈታ ሲገባው እስካሁን መቆየቱ እንዳሳዘናቸው ይገልፃሉ። “ለሌላው ሰው የተሰጠ መብት ለእኔም ልጅ ይሰጠው” ሲሉ ይጠይቃሉ።

እስረኞችን የመፍታት ውሳኔ

ኢሕአዴግ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ በሚል ከታኅሣሥ አጋማሽ ጀምሮ ለ18 ቀናት የሥራ አስፈፃሚ ውይይት ካካሄደ በኋላ ፖለቲከኞችና ሌሎች ሰዎችን ለመፍታት መወሰኑን በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ አማካኝነት ካስታወቀ አምስት ወራት ተቆጥሯል።

የፓርቲውና የመንግሥቱን ውሳኔ ተከትሎ መግለጫ የሰጡት የቀድሞው የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ የማጣራት ሥራውን ጨርሰው እስረኞችን የመፍታቱን ሂደት በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚያጠናቅቁ ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ኾነ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም የኅሊናና የፖለቲካ እስረኞች በሀገሪቱ እንደሌሉ በመግለፅ ሲያስተባብል ቢቆይም ውሳኔው በተላለፈበት በዚህ አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ በምሕረት፣ በይቅርታ፣ ክሳቸውን በማቋረጥና በአመክሮ ታዋቂ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ከእስር እየለቀቀ ይገኛል። እስረኞቹ ከእስር የሚለቀቁት በተለያየ ጊዜ በመሆኑ እስካሁን ምን ያህል ቁጥር ያላቸው እስረኞች እንደተፈቱ በቁጥር አይታወቅም።

የአራቱ ጠበቆች አቤቱታ

ያነጋገርናቸው ጠበቆች እንደሚሉት እስካሁን የቱንም ያህል ቢፈቱም አሁንም ቁጥራቸው የበዛ እስረኞች ከእስር እንዳልተለቀቁ ይናገራሉ። “ከእስር የመፈታት መብት ለሁሉም እኩል ሊሰጥ ይገባል በሚል” ደንበኞቻቸውን ወክለው ለፍርድ ቤትና ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቤቱታ ካቀረቡት መካከል አቶ አለልኝ መኮንን አንዱ ናቸው።

አቶ አለልኝ እስካሁን ሁለት መቶ የሚሆኑ በሽብር የተከሰሱ እስረኞችን ወክለው ፍርድ ቤት ይቀርቡ እንደነበር ገልፀው ከእነዚህ ውስጥ ሥልሳ አምስት እስረኞች ከተፈቱት ተነጥለው እስር ቤት እንደቀሩ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ በሕገመንግስቱ፣ በይቅርታና በምሕረትረት ዐዋጁ መሰረት ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው አቤቱታ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።

አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በጋራ ያቀረቡት ጠበቆች አቶ አለልኝ ምሕረቱን ጨምሮ አቶ ወንድሙ ኢብሳ፣ አቶ ሄኖክ አክሊሊና አቶ አዲሱ ጌታነህ የተባሉ በአጠቃላይ አራት ጠበቆች ናቸው።

አቶ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው በፖለቲካ ምክኒያት በሚታወቁም ሆነ በማይታወቁ እስር ቤቶች ታስረው የሚገኙ እስረኞችን ቁጥር ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው ይላሉ።

ሌላው ጠበቃ አቶ አዲሱ ጌታነህ በወንጀል ሕጉ መሰረት በአንድ ዓይነት ወንጀልና በአንድ መዝገብ የተከሰሱ ተከሳሾች የአንደኛው ክስ ሲቋረጥ የሁሉም አብሮ ሊቋረጥ እንደሚገባ ጠቅሰው “ሕገመንግሥቱም ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው በሚለው መሰረት ለአንደኛው የተለየ መብት ተሰጥቶ ለሌላኛው ደግሞ የሚከለከልበት ሁኔታ ስለሌለ፣ መንግሥትም የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ በሚል ከገባው ቃል ጋራ የሚቃረን ስለሆነ፣መንግሥትም ቃሉን ያክብር ሕጉንም ያስከበር በሚል አዲሱን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቀርበን አነጋግረናቸዋል።” ብለዋል።

በሌላ በኩል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ እስረኞች ከእስር እየተለቀቁ ሲሆን ቤተሰብና ጠበቆቻቸው ግን አሁንም በብዛት ይቀራሉ ሲሉ አቤቱታ ማቅረባቸውንቀጥለዋል። በሌላ በኩል በሸብር ወንጀል ተከሶ ከአምስት ቀናት በፊት ከእስር የተለቀቀ አቶ ቶሎሳ በዳዳ “ በየ እስር ቤቶቹ በጣም ብዙ እስረኞች ይገኛሉ።” ሲል ለአሜሪካድምፅ ተናግሯ።

በቅርቡ የተሾሙት የየፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ መንግሥት እስረኞቹ በተመለከተ የሚሰጠውን ውሳኔ በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጡን የእጅ ስልካቸው ላይተደጋጋሚ ሙከራ አድርገን ስልካቸው ስለማይነሳ ልናገኛቸው አልቻልም። ምላሻቸውን እንዳገኘን ይዘን እንመለሳለን።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG