Your browser doesn’t support HTML5
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ አመራር የነበሩት በቴ ዑርጌሳ፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ መገደላቸውን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ወንድማቸው አቶ ሚሎ ዑርጌሳ፣ አሁንም በመቂ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰሩ መኾናቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል፡፡
በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሟቹ ቤተሰብ አባል፣ የሁለት ልጆች አባት የኾኑት አቶ ሚሎ፣ ፍርድ ቤት ቀርበው የተመሠረተባቸው ክስ ባይኖርም፣ አሁንም በፖሊስ እጅ መኾናቸውን ገልጸዋል። ከግድያው አስቀድሞ አቶ በቴ አርፈውበት ነበር የተባለው ሆቴል ባለቤትም፣ ከወንድማቸው ጋራ እንደታሰረ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘ፣ የአቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር መዋሉ የተነገረው የዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው ሦራ ጅርማ፣ ለሦስት ወራት ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ታስሮ እንደሚገኝ፣ አባቱ አቶ ጅርማ ዓሊ አመልክተዋል።
የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ፣ የሟች አቶ በቴ ዑርጌሳ ግድያ አሁንም በምርመራ ሒደት ላይ መኾኑን ገልጾ፣ ስለ ጉዳዩ ማብራርያ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡