“አፍሪካ ለዓለም የኢኮኖሚ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ኃይል ምንጭ እየኾነች ነው”- ዐቢይ አሕመድ

  • ቪኦኤ ዜና

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አፍሪካ፥ ለዓለም የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ኃይል ምንጭ እየኾነች እንዳለና ዐቅም እንዳላትም እየተገነዘበች እንደምትገኝ፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ዛሬ ቻይና ላይ ተናግረዋል።

ቻይና፥ “ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” በሚል በወጠነችው ተነሣሽነት ላይ ተመሥርቶ በቤጂንግ በሚካሔደው ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “ተገልላ የቆየችው አህጉር አሁን፣ የሕዝቧንና የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም ላይ ናት፤” ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች የዓለም አካባቢዎች የሚካሔዱ ግጭቶች ዳፋ፣ በተለይ አፍሪካን እየጎዳት እንደኾነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የጋራ ደኅንነትን አስመልክቶ በሚዘጋጁ መድረኮች፣ አፍሪካ እጇን አጣጥፋ ተመልካች መኾን እንደሌለባትም አመልክተዋል፡፡

የተሻለ ዓለም፣ የተሻለች ቻይናን ይፈጥራል፤ የተሻለች ቻይና ደግሞ፣ ለዓለም አስተዋፅኦ ታደርጋለች፡፡ የ‘ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ’ ቻይና ለዓለም በሯን እንደከፈተች ማሳያ ነው፤”

ዓለምን፣ በመንገድ እና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች ለማገናኘት ባቀደው የቻይና ተነሣሽነት ላይ በሚደረገው ጉባኤ፣ ከ130 ሀገራት የተውጣጡ መሪዎች እና ተወካዮች ተገኝተዋል።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተናገሩት የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ ከዐሥር ዓመታት በፊት የተጀመረው ፕሮጀክት፣ እስያን ከአፍሪካ እና አውሮፓ ጋራ በመሠረተ ልማት እና በኃይል አውታር ለማገናኘት ያለመ ነው፤ ብለዋል።

የምዕራቡ ዓለም፣ በቻይና ኢኮኖሚ ላይ እየታየ ያለው ጥገኝነት እንዲቀንስ የሚያደርገውን ግፊት፣ ፕሬዝደንት ሺ ተቃውመውታል።

“የተሻለ ዓለም፣ የተሻለች ቻይናን ይፈጥራል፤ የተሻለች ቻይና ደግሞ፣ ለዓለም አስተዋፅኦ ታደርጋለች፡፡ የ‘ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ’ ቻይና ለዓለም በሯን እንደከፈተች ማሳያ ነው፤” ብለዋል ሺ ጂንፒንግ።

ቻይና፣ በመሠረተ ልማት ዘርፍ ለድኻ ሀገራት የምትሰጠው ብድር፣ መክፈል የማይችሉት ዕዳ ውስጥ ጨምሯቸዋል፤ ሲሉ ምዕራባውያኑ ይነቅፋሉ።

ነቀፌታው፥ “ፀረ ቻይና አስተሳሰብ ነው” ስትል ቻይና ትችቱን ታጣጥላለች፡፡