ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ለኢትዮጵያ የተቋረጠው ርዳታ እንዲቀጥል ጥሪ አደረገ

Your browser doesn’t support HTML5

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ለኢትዮጵያ የተቋረጠው ርዳታ እንዲቀጥል ጥሪ አደረገ

ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን(ሜዲሳን ሳን ፍራንቴር) ወይም በእንግሊዘኛው ምኅጻሩ MSF፣ ተቋርጦ የነበረውና ለኢትዮጵያ ሲሰጥ የነበረው የምግብ ርዳታ በአፋጣኝ መልሶ እንዲቀጥል፣ ዛሬ ዐርብ ጥሪ አስተላልፏል።

ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን፣ የምግብ ርዳታው እንዲቋረጥ የተወሰነው፣ “እጅግ አሳሳቢ” የተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ባለበት ወቅት ነው፤ ብሏል።

ለተጎጂዎች የተላከው ርዳታ፣ ላልታሰበለት ዓላማ ውሏል፡፡ በዚኽም፣ የመንግሥት አካላት፥ ተሳታፊ እና ተጠያቂ ናቸው፤ በሚል፣ የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም(WFP) እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት(USAID)፣ ከአንድ ወር በፊት የምግብ ርዳታውን አቋርጠው ነበር። በቅርቡ ግን፣ ውሱን ዐይነት ርዳታዎች መልሰው መለቀቅ እንደሚጀምሩ፣ የአሜሪካ መንግሥት አስታውቋል።

SEE ALSO: የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያቆመውን ርዳታ ከወር በኋላ ሊቀጥል እንደሚችል አስታወቀ

የምግብ ርዳታው ከመቋረጡም በፊት፣ በኢትዮጵያ፣ 20 ሚሊዮን ሰዎች በርዳታ ላይ ጥገኛ ኾነው ይኖሩ እንደነበርና በአንዳንድ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ “እጅግ አሳሳቢ” እንደኾነ፣ ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ገልጿል።

የምግብ ርዳታው መቋረጡ አሳሳቢ ነው፤ ምክንያቱም፣ እንዲቋረጥ የተወሰነው፣ ወትሮውንም በቂ ያልኾነ የርዳታ ምግብ ሥርጭት በነበረበትና በመላ አገሪቱ ያለው ሰብአዊ ኹኔታ አሳሳቢ በኾነበት ወቅት ነው፤”

“የምግብ ርዳታው መቋረጡ አሳሳቢ ነው፤ ምክንያቱም፣ እንዲቋረጥ የተወሰነው፣ ወትሮውንም በቂ ያልኾነ የርዳታ ምግብ ሥርጭት በነበረበትና በመላ አገሪቱ ያለው ሰብአዊ ኹኔታ አሳሳቢ በኾነበት ወቅት ነው፤” ሲሉ፣ የቡድኑ የኢትዮጵያ ዲሬክተር ካራ ብሩክስ መናገራቸውን፣ የኤኤፍፒ ዘገባ ጠቅሷል።

የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA) በበኩሉ፣ በዚኽ ሳምንት እንዳስታወቀው፣ በትግራይ ክልል፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፣ ብሏል። ርዳታው በመቋረጡ ምክንያት፣ ወትሮውንም ተጋላጭ የነበሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ለተጨማሪ ሥቃይ እንደተዳረጉ አክሎ ገልጿል።