በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል ለተራዘመ ረኀብ የተጋለጡ ተፈናቃይ እናቶች እና ሕፃናት ችግር ላይ መሆናቸውን ገለጹ


በትግራይ ክልል ለተራዘመ ረኀብ የተጋለጡ ተፈናቃይ እናቶች እና ሕፃናት ችግር ላይ መሆናቸውን ገለጹ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:37 0:00

በትግራይ ክልል ለተራዘመ ረኀብ የተጋለጡ ተፈናቃይ እናቶች እና ሕፃናት ችግር ላይ መሆናቸውን ገለጹ

በትግራይ ክልል፣ ለተራዘመ ጊዜ ርዳታ ያላገኙ ተፈናቃይ እናቶች እና ሕፃናት፣ ከፍተኛ ችግር ላይ መኾናቸው የትግራይ ሴቶች ማኅበር ገለጸ፡፡

በመቐለ ሰብዓ ካሬ የተፈናቃዮች ማዕከል የሚገኙና ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡ ነፍሰ ጡር የሆኑ ተፈናቃዮች እንደተናገሩት፣ ለሕፃናት እና ነብሰ ጡር እናቶች እየተባለ፣ ርዳታ ወደ ተፈናቃዮች ማዕከል እንደሚመጣ ቢሰሙም፣ ደርሷቸው እንደማያውቅና ከሦስት ወራት በላይ ያለርዳታ አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

መነሻውን በትግራይ ክልል ያደረገው፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጀመረ ከቀናት በኋላ፣ በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም. ጦርነቱን በመሸሽ፣ ከወልቃይት ወረዳ ማይጋባ ወደ መቐለ ከተማ ተፈናቅላ እንደመጣች የምትናገረውን ወይዘሮ ብርጭቆ ሽሙየን ያገኘናት፣ በመቐለ ሰብዓ ካሬ የተፈናቃዮች ማዕከል ነው፡፡

የአምስት ወር ነብሰ ጡር እንደኾነች የገለጸችው ወይዘሮ ብርጭቆ፣ ከልጇ እና ከባለቤቷ ጋራ በማዕከሉ እየኖረች እንደኾነ ተናግራለች፡፡ ለተፈናቃዮቹ እየቀረበ ያለው ሰብኣዊ ርዳታ፣ “በጣም አነስተኛ እና ለረጅም ጊዜ እየዘገየ የሚሰጥ ነው፤” ብላለች፡፡

አክላም፤ “ርዳታ ወደ እኛ የሚመጣው፣ በአምስት ወይም በስድስት ወር አንድ ጊዜ ነው፡፡ ልጅ ይዘኽ ከባድ ነው፡፡ በከፋ ኹኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ ለልጆች የሚመጣ ተጨማሪ ምግብ ካለም፣ ከሚዛን በታች ለኾነ ነው የምንሰጠው፤ ይላሉ። ባለፈው፣ ለነብሰ ጡሮች ተብሎ የመጣውን፣ ከሚዛን በላይ ነሽ፤ ብለው ከልክለውኛል፡፡” ለልጆችም ተመጣጣኝ አልሚ ምግብ መጥቶ ነበር፡፡ ለእርሱ ልጄም፣ “ከሚዛን በላይ ነው” ብለው እንደ እኔው ከለከሉት። ርዳታ ካገኘን ሦስት ወራት አልፎናል፡፡ ከርዳታው የተወሰነ ሸጠን፥ ለወፍጮ፣ ለጨው እና ለበርበሬ መግዣ እንጠቀምበታለን፡፡ በጣም ከባድ ኹኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡” ብላለች።

የትግራይ ሴቶች ማኅበር ሥራ አስከያጅ ወይዘሮ አበባ ኃይለ ሥላሴ፣ በተፈናቃዮች ማዕከል፣ ሴቶች በእኩልነት ርዳታ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ የሴቶች አደረጃጀት ቢፈጠርም፣ በርዳታ ማከፋፈል ረገድ፣ ኢፍትሐዊነት ይታያል፤ ብለዋል::

“ብዙ ኢፍትሐዊ ሥራዎች እየተፈጸሙ ቆይተዋል፡፡ ነብሰ ጡር ሴቶች ርዳታ ማግኘት ሲገባቸው ሳይሰጣቸው ይቀራል፡፡ የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያን ሳይቀር ወንዶች የሚወስዱበት አጋጣሚም ታይቷል” ያሉት ወይዘሮ አበባ “ይህ እንዲስተካከል፣ ከመንግሥታዊ አመራሮች ጋራ በተደጋጋሚ ተወያይተናል፡፡ የተፈናቃዩ ብዛት እና የሚቀርበው ርዳታ መጠን የሚመጣጠን አይደለም፡፡ በየአራት ወሩ የሚመጣው ርዳታም፣ የማይደርሳቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ይባስ ብሎ፣ አሁን ደግሞ በጠቅላላ ርዳታው ተቋርጧል፡፡ በዚኽም፣ ብዙ እናቶች፥ ወደ ጎዳና ወጥተው እየለመኑ ናቸው፡፡ በጣም በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ለተፈናቃዮች ርዳታ ከተከፋፈለ ወራት እንደተቆጠሩና መጠኑም አነስተኛ እንደኾነ ነው፣ በመቐለ ሰብዓ ካሬ ተፈናቃዮች ማእከል ተጠልላ እንደምትገኝ የገለፀችው ወይዘሮ ብርጭቆ፤ “ሥራ እንዳንሠራ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ገንዘብ የለንም።ባንክም ቢከፈት ተቀማጭ የለንም፡፡ በዚኽ ማዕከል ርዳታ የሚሰጠው፣ በረኀብ ከተሠቃየን በኋላ ነው፡፡ በአስከፊ ኹኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡" ብላለች።

ለሕፃናት እና ነብሰ ጡር እናቶች እየተባለ፣ ርዳታ ወደ ተፈናቃዮች ማዕከል እንደሚመጣ እንደሚሰሙና የተናገረችው ወይዘሮ ብርጭቆ፣ ነገር ግን ለእኛ ተሰጥቶን አያውቅም፤ ብላለች፡፡

“ለእርጉዞች እና ለወለዱ እናቶች፣ ርዳታ መጥቷል ሲባል እንሰማለን፡፡ እኔ አሁን የአምስት ወር እርጉዝ ነኝ፡፡ እስከ አሁን ያገኘኹት ነገር የለም፡፡ ነብሰ ጡር ሴት፣ የተመጣጠነ ምግብ ልታገኝ ይገባት ነበር፡፡ ኾኖም አላገኘንም፡፡” ስትልም ወደ ነበረችበት ማይጋባ ተመልሳ የቀድሞ ኑሮዋ ዳግም ለመጀመር እንደምትናፍቅ ወይዘሮ ብርጭቆ ተስፋ ታደርጋለች፡፡

የትግራይ ሴቶች ማኅበር ሥራ አስከያጅ ወይዘሮ አበባ ኃይለ ሥላሴ፣ ሥርጭቱ የተቋረጠው ሰብአዊ ርዳታ እንዲቀጥል መደረግ ይኖርበታል፤ እንዲሁም ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ሊመለሱ እንደሚገባ ተናግረዋል::

በአንጻሩ፣ በትግራይ ክልል፣ ለአስቸኳይ ምግብ ፈላጊዎች የተላከ፣ 86ሺሕ ኩንታል ስንዴ፣ በተለያዩ አካላት እንደተዘረፈ፣ በክልሉ የተመዘበረ የርዳታ እህል አጣሪ ኮሚቴ፣ በዚኽ ሳምንት ገልጿል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ እና የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ሓላፊ ሌተናል ጀነራል ፍሥሓ ኪዳኑ፣ ለክልሉ ብዙኃን መገናኛ በሰጡት ማብራርያ፣ በምዝበራው፥ የኤርትራ ኃይሎች፣ በፌዴራሉ መንግሥት ተሹመው የነበሩ የጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች እና የክልሉ መዋቅር መሳተፋቸው ተናግረዋል፡፡ ኮሚቴው ባካሔደው ጥናት፣ ከስንዴ በተጨማሪ፣ ከ215 ሺሕ ሊትር በላይ ዘይት እና ከሰባት ሺሕ ኩንታል በላይ የጥራጥሬ እህሎች መዘረፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በምዝበራ ድርጊቱ የተጠረጠሩ 186 ግለሰቦች መኖራቸውንና ከእነርሱም ሰባቱ በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ የማጣራት ሒደቱም እንደቀጠለ መኾኑን ሓላፊው ገልጸዋል፡፡

ለኢትዮጵያ የሚላከው የምግብ ርዳታ፣ “አስቸኳይ ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች እየደረሰ አይደለም፤” በሚል፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት/USAID/ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም/WFP/፣ አመቺ እና አስተማማኝ የርዳታ ሥርጭት ሥርዐት እስኪዘረጋ ድረስ፣ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የእህል ርዳታ ማቋረጣቸውን ባለፈው ሳምንት ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG