በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ የምግብ ርዳታ መቋረጡ “ሚሊዮኖች ተረጂዎችን መቅጣት እንደኾነ” አስታወቀች


የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ለገሰ ቱሉ
የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ለገሰ ቱሉ

ለኢትዮጵያ የሚላከው የምግብ ርዳታ፣ “ለተረጂዎች እየደረሰ አይደለም” በሚል፣ ሁለት ዋና ዓለም አቀፍ ለጋሾች፣ የእህል ርዳታ ለማቋረጥ የወሰዱትን ርምጃ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሟል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ለገሰ ቱሉ፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት እና ተራድኦ ድርጅት/USAID/ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም/WFP/ የወሰኑት ውሳኔ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚቀጣ ነው፤ ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የርዳታ ተቋም የኾነው ዩኤስኤይድ፣ ርዳታ በሚደርስበት መንገድ ዙሪያ፣ አመቺ እና አስተማማኝ የአሠራር ለውጥ እስኪደረግ ድረስ፣ የምግብ ርዳታ ሥርጭቱን ማቆሙን አስታውቆ ነበር። ከአንድ ቀን በኋላ ደግሞ፣ ተመሳሳይ ውሳኔውን ያሳወቀው የዓለም ፕሮግራም እንዲሁ፣ ለኢትዮጵያ ተጎጂዎች ሲያሠራጭ የቆየውን የምግብ ርዳታ፣ “ስርቆት በመንሰራፋቱ” ምክንያት ለጊዜው ማቆሙን አስታውቋል።

ውሳኔው፥ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሔደው ጦርነት፣ በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ በተከሠተው እና ሶማሊያንና የኬንያን የተወሰኑ ክፍሎችን በአጠቃው ድርቅ ምክንያት፣ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ይጎዳል።

ባለፈው ወር፣ ዩኤስኤይድ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ለትግራይ የሚላከው ርዳታ ለገበያ እንደሚቀርብ ከደረሱበት በኋላ፣ የምግብ ርዳታ እንዲቆም ማድረጋቸውን አስታውቀው ነበር። ኾኖም፣ ሁለቱም ተቋማት፣ የርዳታ እህሉን ከተረጂዎች ወስደው ለገበያ በማቅረብ ተጠያቂ የኾኑትን አካላት ለይተው አልገለጹም።

የመንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ፣ ርዳታውን የማቆሙ ውሳኔ “ፖለቲካዊ ነው” ያሉ ሲኾን፣ “መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ተቀባይነት የለውም፤” ብለዋል።

አክለውም፤ ”በጋራ ለማጣራት ስምምነት ከተደረሰ በኋላ መግለጫው ቀድሞ መሰጠቱ ትክክል አይደለም፤” ብለዋል።

መንግሥት፣ ባለፈው ዐርብ፣ ከዩኤስኤይድ ጋራ በመኾን በሰጠው መግለጫ፣ እጅግ አሳሳቢ የኾነውን የምግብ ርዳታ፣ ለተጎጂዎች እንዳይደርስ የማድረጉን ክፍተት ለመፍታት ቁርጠኝነቱን ገልጿል።

በድርቅ እና በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት፣ በኢትዮጵያ፥ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ሰዎች፣ የምግብ ርዳታ ጠባቂዎች መኾናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (UN-OCHA) ባለፈው ግንቦት ያወጣው መረጃ ያሳያል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ፣ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን የምታስተናግድ ሲኾን፣ አብዛኞቹ፥ ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የመጡ ናቸው። ከሚያዝያ ወር አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ፣ በሱዳን የተፈጠረውን ግጭት የሸሹ ወደ 30ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

XS
SM
MD
LG