አቶ መለስ ከዜጎች ለተሰበሰቡ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት የኢህአዴግ የምረጡኝ ዘመቻን ተቀላቀሉ

  • እስክንድር ፍሬው
በአባሎቻቸው ላይ የሚቀርቡ ውንጀላዎች በተጨባጭ በፍርድ ቤት ከተረጋገጡ አባሉ ከድርጅቱ እንደሚባረርና የህግ ዕርምጃውም ተግባራዊ እንደሚሆን አቶ መለስ ተናግረዋል

ከ600 በላይ ለፓርቲው ፅህፈት ቤት በስልክ የደረሱ ከተባሉ የህዝብ ጥያቄዎች ቀዳሚውን ባስተናገዱበት የጥያቄና መልስ ሂደት፥ የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሊቀ መንበር መለስ ዜናዊ ተጠያቂ፤ የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሴኮ ቱሬ ጌታቸው ደግሞ ጠያቂ ሆነው ቀርበዋል።

በተለያዩ ክፍሎች በደሎች ደረሱብን በሚል በተቃዋሚ ዕጩዎች የሚቀርቡ ትችቶች መሠረት የሌላቸው መሆናቸውን መለስ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

የፓርቲው የተለያዩ ልሳኖች በተከታታይ ለአባላት ሥልጠናዎች መሠጠታቸውን የሚናገሩት አቶ መለስ፤ በጥረታቸው ሊገጥም ይችል የነበሩ ችግሮችን መከላከል መቻላቸውን አስረድተዋል።

ይሄም ሆኖ ግን ፍፁም ነን፤ ማለታችን አይደለም ያሉት መለስ በአባሎቻቸው ላይ የሚቀርቡ ውንጀላዎች በተጨባጭ በፍርድ ቤት ከተረጋገጡ ግን አባሉ ከድርጅቱ እንደሚባረርና የህግ ዕርምጃውም ተግባራዊ ይሆናል፤ ብለዋል።

በተግባር ስኬታማ መሆን ብቻ ሳይሆን በንድፈ ሃሳብ ደረጃም እንደሚባለው ፓርቲያቸው የሚከተለውን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር «የሶሻሊዝም ፍልስፍና አይደለም፤ ልማታዊ እንጂ፤» ሲሉ ተከላክለዋል።

መለስ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ፍልስፍናዊና ተግባራዊ ስኬት ለማስረገጥ የድርጅታችንና የመንግስታችን ወዳጅ ያሏቸውን የቀድሞ የዓለም ባንክ ዋና የምጣኔ ሃብት ባለሞያና የኖቤል ተሻሚ ፕሮፌሰር ጆሴፍ ስቲልጊትስን በዋቢነት አንስተዋል።

በጥያቄና መልሱ ወቅት ፕሮፌሰሩ በአንድ ወቅት የፕሬዝዳንት ክሊንተን የምጣኔ ሃብት አማካሪም ጭምር እንደነበሩ ያነሱት አቶ መለስ፤ ይሄንን አቅጣጫ መደገፍ ብቻ ሳይሆን ያቀነቅኑም እንደነበር ገልጠዋል።

በትይይው ግን የኒዮ ሊበራሊዝም አቅጣጫ «ለአፍሪካ ሲጠቅም አልታየም፤» ሲሉ መለስ የፓሪቲያቸውን ዘመቻ የተቀላቀሉበትን የመጀመሪያ ዙር ቃለ ምልልስ ቋጭተዋል።