ከፊታችን ጥር 12/2009 ዓ.ም እስከ ጥር 11/2013 ዓ.ም. ለሚመጡት አራት ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስን መንግሥት የሥራ አስፈፃሚ ክንፍ የሚመራውን አርባ አምስተኛውን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት፤ ዋና ሥራ አስፈፃሚና የሃገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ለመምረጥ ለሚደረገው ፉክክር ሁለቱ ዋና ዋና ፓርቲዎች በየራሣቸው የሚወክሉትን ዕጩ ለማውጣት ትንቅንቁ ቀጥሏል፡፡
በሪፐብሊካን ፓርቲው በኩል በ17 ተፎካካሪዎች መካከል የተጀመረው ሩጫ አሁን ወደ አራት የፍፃሜ አቅራቢያ ሯጮች ደርሷል፡፡
በባለ ቢሊዮኖች ዶላሩ ቱጃር፣ የቤቶች አናፂና ሻጭ፤ የሆቴሎች፣ የቁማር ቤቶች፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ባለቤት፣ እስከቅርብ ጊዜም የቴሌቪዥን ፕሮግራም መሪ በነበሩት በዶናልድ ጄ ትራምፕ መሪነት የቴክሣስ ሴናተርና የፍሎሪዳ አቻቸው ቴድ ክሩዝ እና ማርኮ ሩቢዮ፣ እንዲሁም የኦሃዮው ጠቅላይ ገዥ ጃን ኬሲክ ተከታትለው ወደ ፍፃሜው እየገሰገሱ ነው፡፡
በዴሞክራቲክ ፓርቲው በኩል ደግሞ ሂላሪ ክሊንተን በሚመሩት ሩጫ ከጠንካራው ተፎካካሪያቸው በርኒ ሳንደርስ ጋር ተናንቀዋል፡፡ የሜሪላንድ ጠቅላይ ግዛት የቀድሞ አገረ ገዥ ማርቲን ኦማሊ መንገዱ ሻካራ ስለሆነባቸው እራሣቸውን በጊዜ አሰናብተዋል፡፡
የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ ለመሆን 2383 የፓርቲ እንደራሴዎችን ድምፅ ማግኘት ያስፈልጋል፤ ሂላሪ ክሊንተን ግማሹን ያህል ጨብጠዋል እስከአሁን፡፡ 1237 ይዘዋል፡፡ ሳንደርስ ደግሞ 571 እንደራሴዎች ወይም ዴሌጌቶች አሏቸው፡፡
የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ለመሆን 1237 የፓርቲ እንደራሴዎችን ድምፅ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡
እስከዛሬ በተሰጡት ድምፆች ቀዳሚው ዶናልድ ትራምፕ 458፣ ተከትለዋቸው ያሉት ክሩዝ 359፣ ሩቢዮ 151፣ ኬሲክ 54 ዴሌጌቶችን ወይም የፓርቲ እንደራሴዎችን ተከፋፍለዋል፡፡
ይህንን የዘንድሮውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚኪስ ፕሮፌሰር የሆኑትን ዶ/ር ሰይድ ሃሰን ይገመግሙታል፡፡
ከፕሮፌሰር ሰይድ ሃሰን ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5